Friday, May 27, 2016

የራስ መንግስት መመስረትና ነጻነት ምንና ምን ናቸው? – (ሊያነቡት የሚገባ)

ዛሬ መጻፍ የፈለግሁት በእንግሊዝኛ Independence እና Freedom ስለሚባሉ ሁለት የፖለቲካ ትግል መሰረታዊ ፍሬ ሀሳቦች ነው። ወደ አማርኛ ስንመልሳቸው Independence ማለት «ተለይቶ የራስ መንግስት መመስረት» ወይንም «የራስ አገር መፍጠር» ማለት ሲሆን Freedom ማለት ደግሞ በሚኖሩበት አገር ውስጥ ነጻነት ማግኘት ወይንም ነጻ መሆን ማለት ነው። ስለዚህ ለIndependence የሚደረግ የፖለቲካ ትግል ማለት ተለይቶ የራስ መንግስት ለመመስረት ወይንም የራስ አገር ለመፍጠር የሚደረግ ትግል ማለት ሲሆን ለFreedom የሚደረግ ትልግ ማለት ደግሞ በሚኖሩበት አገር ውስጥ ለነጻነት ወይንም ነጻ ለመሆን የሚደረግ ትግል ማለት ነው

Tensaye

በአገራችን ላለፉት ሃምሳ አመታት በብሄረሰብ ማንነት የተሰባሰቡ የዘር ድርጅቶች ያደረጉት የLibration ፍልሚያ [ዛሬም እያደረጉት ያለው የፖለቲካ ቁማር ጭምር] ለነጻነት የተደረገ ንቅናቄ ሳይሆን ተለይቶ የራስን መንግስት ለመመስረት ወይንም የራስን አገር ለመፍጠር ያካሄዱት ትግል ነው። በመሰረቱ ለነጻነት መታገል በብሔረሰብ መደራጀትን አይጠይቅም። በብሄረሰብ ተደራጅቶ መታገል ሊያስገኘው የሚችለው ብቸኛ ግብ የራስ መንግስት መመስረት ወይንም የራስ አገር መፍጠር ብቻ ነው። በብሄረሰብ ተደራጅቶ የራስ መንግስት ለመመስረት መታገል ነጻነትን ሊያጎናጽፍ አይችልም። የራስ አገር ለመመስረት በሚደረግ ትግል የኦሮሞ ገበሬ የመሬት ባለቤት ሊሆን አይችልም። የኦሮሞ ገበሬ የመሬት ባለቤት ሊሆን የሚችለው ለነጻነት በሚደረግ ትግል ብቻ ነው። የራስ አገር ለመመስረት በሚደረግ ትግል የመሬት ባለቤት መሆን የሚቻል ቢሆን ኖሮ ዛሬ የትግራይና የኤርትራ ገበሬ የመሬት ባለቤትና ባለ መብት በሆነ ነበር።
የአገራችን የብሔረሰብ ድርጅቶች ትልቁ ስኬት እናቱ ገበያ የሄደችበትን የብሔረሰባቸው አባል እናትህ ሞታለች ብለው ማስለቀስ መቻላቸውና «ጭቆና እየደረሰበኝ ያለው ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች [ማለትም ጨቋኞቹ] የብሔረሰቤ አባላት ስላልሆኑ ነው» ብሎ የሚያምን ትውልድ መፍጠራቸው ብቻ ነው። ይህን ስብከታቸውን ለማንበርም «ተጨቆነ» በሚሉት ብሔረሰብና «ጨቋኝ» ነበር ባሉት ብሔረሰብ መካከል ምንም አይነ ግንኙነት ወይንም ዝምድና እንደሌለ የፖለቲካ ታሪክ ፈጥረዋል። «ተጨቆነ» በሚሉት ብሔረሰብ መካከልና «በጨቋኙ» ብሔረሰብ መካከል የነበሩትን ትስስሮችና አንድ የሚያደርጉትን ክሮች ሁሉ በጥሰዋል። በአንድነቱ ጊዜ «የኔ ብሔረሰብ አባላት ናቸው» የሚሏቸው ሰዎች የነበራቸውን አስተዋጽኦ አሳንሰዋል፤ አኮስሰዋል። ሰዎቹንም ጭቃ ቀብተዋቸዋል። የነበራቸውን ሚናም እንዳልነበረ አድርገውታል። ራስ አበበ አረጋይ፣ ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ፣ገረሱ ዱኪ፣ ይልማ ደሬሳ፣ ራስ መንገሻ ስዩም፣ ራስ ስዩም መንገሻ፣ ሀረጎት አባይ፣ ሎሬንሶ ታዕዛዝ ወዘተ የራስ አገር ለመፍጠር በታገሉና አሁንም እየታገሉ ባሉ የዘር ፖለቲከኞች ፕሮፓጋንዳ ዶግ አመድ ሆነዋል።
ዛሬም ድረስ የአገራችን የዘር ድርጅቶች «የምንጨቆነው ጨቋኞቹ የኛ ብሄረሰብ አባላት ስላልሆኑ ነው» የሚሉት የዘር ቅስቀሳ የራሳቸውን አገር ለመመስረት ሲሉ የብሔረሰቦቻቸው አባላት የሆኑ ወገኖቻቸው ትግል እንዲያደርጉ የሚያነሳሱበት ዋነኛ ዘዴያቸው ነው። ተከታዩም ስላልነቃ ጥሪያቸውን ሰምቶ አብሯቸው ይጎተታል። እነዚህ የራሳቸውን አገር ለመመስረት የሚታገሉ የዘር ድርጅቶች «ስልጣን ላይ ያሉት ጨቋኞች የሚጨቁኑኝ የብሔረሰቦቻችን አባላት ስላልሆኑ ነው» የሚለውን ያረጀ ስብከታቸውን የበለጠ ለማሳመን ደግሞ በአንድነቱ ጊዜ የነበሩ የብሔረሰባቸው አባላት የሆኑ ልሂቃን ለአገራቸው ሲሉ ያደረጉትንም አዲስ ትርጓሜ በመስጠት ስራዎቻቸውንና ሰዎቹን አሳንሰዋቸዋል።
ባለ ቅኔው ጸጋዬ ገብረመድህን የዚህ የማሳነስ ዘመቻ ሰለባ ነው። ባለ ቅኔው ጸጋዬ «በማናቸውም የአለም ህዝብ ታሪክ ውስጥ የሚገኝ የየአገሩ ወንዝ ጉዞ የየአገሩ ሰፊ ህዝብ የየትውልድ ጉዞ ተምሳሌት ሆኖ ይቀረጻል» በማለት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት እንደ አባይ፣ አዋሽ፣ ዋቢ ሸበሌ፣_ ተከዘ፣ መረብና ሌሎቹንም ወንዞች ከኢትዮጵያ አፈጣጠር ጀምሮ የኢትዮጵያን ታሪክና ትውልዶች ጉዞ በተምሳሌትነት ለማሳየት በኢትዮጵያውያንና በባዕድ የስነጽሁፍ ሰዎች ሳይቀር እንደተቀረጹ ያስረዳና ከባዕድ አገራትም ኤፍራጦስና ጤግሮስ በሜሶፖታሚያ፤ ቴምስ በእንግሊዝ፤ ሚሲሲፒ በአሜሪካና ዶን በሩሲያ የየዘመኑ ታላላቅ ጸሀፍት ዘንድ የየአገራቱን ህዝብ ታሪክና የየትውልድ ጉዞ ለማሳየት በተምሳሌትነት እንደቀረቡ አውስቶ እሱም በብዕሩ የኢትዮጵያን ታሪክና የየትውልድ ጉዞ በአዋሽ ተምሳሌትነት የጻፈውን አስደማሚ ግጥም ኦነጋውያን «ስለኦሮሞ ህዝብ እጣ ፈንታና መጻኢ እድል» የጻፈው አድርገው በማሳነስ አዲስ ትርጓሜ ሰጥተውበታል።
ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ የራሳቸውን አገር ለመመስረት የሚታገሉ የዘር ድርጅቶች በአንድነቱ ጊዜ የነበሩ አንዳንዶቹን የብሔረሰባቸው አባላትና አስተዋጿቸውን ደግሞ እንዳላዩ አልፈዋቸዋል። የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ የዘፈናቸውን በርካታ የኦሮምኛ ዘፈኖች፤ዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግስት ደጃፍ ላይ ቁጭ ብለው እነ ጥላሁን ገሰሰና ብዙነሽ በቀለ የዘፈኑትን ያንን ሁሉ የኦሮምኛ ዘፈን ኦነጋውያን እንዳልነበረ ቆጥረውታል። ሻዕብያም በበኩሉ ከጥላሁን ገሰሰና ብዙነሽ በቀለ እኩል የትግርኛ ዘፈናቸው ሸክላና ካሴት ይሸጥላቸው የነበሩትን እነ በረኸት መንግስተዓብንና ትበርህ ተስፋሁነኝን እንዳልነበሩ፤ በኢትዮጵያ ማዕቀፍም ያ ሁሉ ነገር እንዳነበረ በመቀስቀስ በውሸት አገር ፈጥሯል።
የራሳቸውን አገር ለመመስረት የሚታገሉ የዘር ድርጅቶች ከዚህ በከፋም በአንድነቱ ጊዜ የነበሩና እስከመጨረሻው ድረስ በኢትዮጵያዊነት አቋማቸው ጸንተው የቆሙትን የብሔረሰባቸው አባላት ስለኢትዮጵያ ያደረጉትን ሁሉ የከሀዲዎች ድርጊት አድርገው አጣጥለውታል። ራስ ጎበና ዳጨ፣ ጄኔራል ጃጋማ ኬሎና አስፍሀ ወልደ ሚካዔል የዚህ የዘረኞች የከሀዲነት ክስ ሰለባዎች ናቸው። በቤተ ኦነግ «ጎበና» የሚለው ስም ሲጠራ የክህደት፣ የጸረ ኦሮሞነትና የጥፋት ተላላኪነት መገለጫ ሆኗል። ይህ ሁሉ ትርክት «የምንጨቆነው ጨቋኞቹ የኛ ብሄረሰብ አባላት ስላልሆኑ ነው» የሚለውን በብሔረሰቦቻቸው አባላት ላይ አስርጸው የራሳቸውን አገር ለመመስረት የሚያደርጉትን ትግል ለማቃናት ነው።
ዛሬ ዛሬ ደግሞ «ብዝሀነትን» ወያኔና ኦነግ ከደደቢት በረሀና ከሞቃድሾ ቤተ መንግስት ስበው ያመጡት አንዳች አዲስ ጽንሰ ሀሳብ ሆኖ እየተሰበከ ይገኛል። ላስተዋለው ግን በተለይ በኢትዮጵያ ንጉሳዊ ቤተሰብ ውስጥ ብዝሀነት አዲስ አይደለም፤ በቤተ መንግስት ደግሞ በጉልህ ይታይ ነበር። አዎ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በቤተ መንግስታቸው ከነ ራስ አበበ አረጋይ፤ከነ ራስ ስዩም መንገሻ፤ ከነ ዋቆ ጉቱ፣ ከነ ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፤ ከነ ራስ መስፍን ስለሺ፣ ከነ ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ከነ ተድላ ባይሩ፣ ከነ ሐረጎት አባይ፣ወዘተ ጋር ሲገናኙ በአማርኛ ያወሩ ነበር። እንኳን ያንድ አገር ሰዎች የተለያዩ አለም መሪዎች እንኳ ዋይት ሀውስ ሲሄዱ ከአሜሪካን ፕሬዝደንቶች ጋር የሚነጋገሩት በእንግሊዝኛ ነው። ሁለት ሰዎች ይግባቡ ዘንድ በአንድ ቋንቋ ማውራታቸው ግድ ነው። «የብዝሀነት አባት» ተደርጎ በካድሬዎቹ የሚሰበክለት መለስ ዜናዊም ከነ አባዱላ ገመዳ፣ ከነ አባተ ኪሾ፣ ከነ ኩማ ደመቅሳ፣ ከነ አብዱል መድጅ ሑሴን፣ ከነ ግርማ ብሩ፣ ከነ ጁኔይድ ሳዶ፣ከነ አልማዝ መኩ፣ ከነ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግስት ሲገኛኝ የሚያወራው በአማርኛ ነበር።
ሌንጮ ለታም በመስ ዜናዊ ቦታ ቢቀመጥ ኖሮ ከነ ስዬ አብርሀ፣ ከነ ካሱ ኢላላ፣ ከነ አብዱል መጂድ ሑሴን፣ ከነ መብርሀቱ ገብረሕይወት፣ከነ ተኽሉ ተኽላይ ጋር ሲገናኝ የሚያወራው በአማርኛ ነበር። ልዩነቱ ወንበሩ ላይ የሚቀመጡት ሰዎች እንጂ የብዝሀነት አይደለም። ሆኖም ግን ታሪክ የሚጻፈው በየዘመኑ አሸናፊዎች ነውና የኢትዮጵያ ብዝሃነት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግስት ያልነበረ፤ በመለስ ዜናዊ ቤተ መንግስት ግን ከደደቢት ተስቦ እንዳዲስ የተጀመረ ተደርጎ ተጻፈ። ዛሬ በአፍ የሚሰበከው «ብዝሀነት» የነጻነት ፍቺ ቢሆን ኖሮ «ብዝሃነት ተከበረ» በተባለበት በመለስ ዜናዊ ዘመነ መንግስት የኦሮምያ ምስለኔ ከነበረው ከኦሮሞው አባዱላ ገመዳ በላይ በኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት የሸዋ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ የነበሩት ኦሮሞው ራስ መስፍን ስለሺ የተሻለ ነጻነት አይኖራቸውም ነበር።
የራሳቸውን አገር ለመመስረት የታገሉት ኤርትራውያን ለነጻነት ስላልታገሉ ለሰለሳ አመታት ያህል ታግለው የራሳቸውን አገር መመስረት ከቻሉ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበራቸውን ነጻነት ጭምር ለኢሳያስ አስረክበው ከሰላሳ አመት የበረሀ ትግል በኋላ ያገኙት ነገር ቢኖር ነጻነት ሳይሆን በባርነት የሚኮሩበት የራስ ቴምብርና ባንዲራ ብቻ ነው። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ኤርትራ ነጻ ፓርላማ ነበራት። ኤርትራ ወደናት አገሯ ከተቀላቀለች በኋላም ኤርትራውያን እንደራሴዎች በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ እንዴት ንቁ ተሳታፊ እንደነበሩ የአስመራ ከንቲባ የነበሩት የደጃዝማች ሐረጎት አባይ ልጅ ኤርትራዊው ስዩም ሀረጎት «The Bureaucratic Empire Serving Emperor Haile Selassie» በሚል ርዕስ በጻፉት ድንቅ መጽሀፋቸው በሰፊው አቅርበውታል። ኤርትራውያን ጫካ የገቡት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበራቸው ነጻነት አነሰን በሚል ነበር።
የራሳቸውን አገር ለመመስረት ባደረጉት ትግል ግን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበራቸውን መብትም ከናካቴው አጥተዋል። «የነበራቸው ነጻነት አነሰን፤ ይጨመርልን» ብሎ ዱር ቤቴ ያለው የኤርትራ ህዝብ ለሰላሳ ዓመታት ያህል ታግሎ የራሱን መንግስት ሲመሰርት የነበረውንም ነጻነት አጣ። የኤርትራ ህዝብ ለሰላሳ ዓመታት ያህል የራስ አገር ለመመስረት ባደረገው ተጋድሎ የነበረውን ነጻነት ሽጦ ያገኘው ጥቅም የኢሳያስ ቴምብርና ባንዲራ ብቻ ነው። ለኤርትራውያን ይህ የኢሳያስ ቴምብርና ባንዲራ ከመለስ ዜናዊ ቴምብርና ባንዲራ ጋር በምን እንደሚለይ አላውቅም። እንዴውም በዘር ሀረግ ከኢሳያስ በላይ መለስ ዜናዊ ኤርትራዊ ነው።
የሆነው ሆኖ ነጻነት የራስ አገር ለመመስረት በሚደረግ ትግል አይገኝም። እንዴውም በተግባር እንደታየው ከሆነ የራስ አገር ለመመስረት የታገሉ ህዝቦች የነበራቸውን አንጻራዊ ነጻነት አጥተዋል። ኤርትራውያን የዚህ ትራጀዲ ዋና አብነቶች ናቸው። ኦነግ በሚያደርገው የራስ አገር የመመስረት ትግልም ቢሆን የሚገኘው የነጻነት «ትሩፋት» ኤርትራውያን ካጋጠማቸው የከፋ፤ ምናልባትም ሶማሊያ ውስጥ እንደተከሰተው አይነት የርስ በርስት መተላለቅ ሊሆን እንደማይችል ዋስትና የለም። ኦነግ የሚመሰርታት ኦሮምያ የምትባለዋ «አገር» ከሶማሊያ የከፋ ሁኔታ ሊያጋጥማት የማትችልበት ዋስትና እስካሁን ያቀረበ ኦነጋዊ አላጋጠመኝም። ዛሬ ኦሮምያ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለች ብቻ የማይታይ የሚመስለው የጎሳ፣ የባህል፣ የርዕዮተ አለምና የእምነት ልዩነቶች ኦነግ የኦሮሞ አገር ሲመሰርት ያቆጠቁጡና እንደሶማሊያ ጎሳዎች የፖለቲካ መሳሪያ ሆነው እንደማያገለግሉ ዋስትና የለም።
አንዳንዶቹ ኦነጋውያን ያለ ኦሮምያ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ይላሉ። ያልገባቸው ነገር ቢኖር ያለ ኢትዮጵያ ኦሮምያም እንደማትኖር ነው። ኢትዮጵያ በመኖሯ ኦሮምያ ውስጥ ያሉት የጎሳ፣ የባህል፣ የርዕዮተ አለምና የእምነት ልዩነቶች የግጭትና የርስ በርስ መከሳከስ መንስዔዎች አልሆኑም። ኢትዮጵያ ባትኖር ኦሮምያ ውስጥ ያሉት የጎሳ፣ የባህል፣ የርዕዮተ አለምና የእምነት ልዩነቶች ገንትረው እንደ ሶማሊያ የመከሳከሻ፣ የመፈረካከሻና የሞት ማንገሻ መሳሪያዎች አለመሆናቸው ዋስትና የለም። ስለዚህ የኦሮምያ መኖር ለኢትዮጵያ አስፈላጊ የሆነውን ያህል የኢትዮጵያ መኖርም ኦሮምያ እንደሶማሊያ እንዳትሆን ትልቅ ዋስትና ነው። ይህን የሚጠራጠር ካለ ያስብበት።

የባሮ ቱምሳ ሞት ለዚህ አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ክርስቲያኑ ባሮ ቱምሳ በጭንቅላቱ የሳለውን የኦሮሞ አገር ይዞ ለመታገል ሀረር ሲመሽግ የእስላሚክ ኦሮምያ ታጋዮች «ክርስቲያን ነጻ አያወጣንም» በሚል አርደውታል። ኢትዮጵያ ባትኖር ኖሮ በበባሮ ላይ የደረሰው በሌንጮ ለታና በገላሳ ዲልቦ ላይ ላለመድረሱ ዋስትና የለም ነበር። በሌንጮ ለታና በገላሳ ዲልቦ ላይ የሚደርሰው በኦሮሞ ክርስቲያኖችና በዋቄ ፈታ ስርዓት አማኞች ላይ ላለመድረሱ ዋስትና የለም።
ዛሬ ላይ የኦነግን ሀሳብ የሚያቀነቅኑ የኦሮሞ ኤሊቶች በተለይ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን በሚያራምዱ ምሁራን ላይ የሚያካሂዱትን የጥላቻ ፖለቲካና መረን የለቀቀ ቀፋፊ ንግግር ለተመለከተ ኦነግ በለስ ቢቀናው በሚፈጥረው አገር የሚገዛቸው ህዝቦች እድል ፈንታ ከኤርትራውያን ይዞታ የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። የሚገርመው ግን አብዛኛው የነዚህ ዘረኛ የኦነግ ኤሊቶች ተካታይ የሆኑ ወጣት ኦሮሞዎች ዘረኞቹ ኦነጋውያን ኢትዮጵያዊ ብሔርተኞችን ለማሸማቀቅ የጥላቻ መርዝ በሚተፋው ምላሳቸው የሚረጩትን መረን የለቀቀ ስድነት እያዩ «አበጃችሁ፤ ጎሽ፤ ጀግኖቻችን ናችሁ» ማለታቸው ነው። አላወቁትም እንጂ ይህ መርዘኛ ምላስ ነገ በለስ ቀንቶት አዲስ አገር ሲመሰርት ቀድሞ የሚበላው እነሱን ነው። ኢሳያስ አፈወርቂ ሻዕብያን ለመንግስትነት ከማብቃቱ በፊትም ጫካ እያሉ «ማንካ» በሚባለው የሻዕብያ «የህንፍሽፍሽ» እንቅስቃሴ በሃሳብ የተለዩትን የትግል አጋሮቹ የሆኑትንና በቀማዳዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የፊት ተዋናይ የነበሩትን እነ ዮሀንስ ስብዓቱን በሀሳብ ስለተለዩ ብቻ ገድሏቸዋል። ዮሀንስ ስብዓቱን ግን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት ታስሮ በይቅርታ ምህረት ተሰጥቶት ከእስር የተነቀቀ ነበር።
እንግዲህ ይታያችሁ ዮሀንስ ከኢሳያስ በሀሳብ ስለተለየ ለነጻነት ታገልሁ በሚለው ኢሳያስ ተረሸነ። ዮሀንስ ስብዓቱ ግን ዲሞክራሲ የለበትም በተባለበትና ዘመንና «ሪያክሽነሪ» በተባሉት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ምህረት የተሰጠው ነበር። ኢሳያስ አፈወርቂ በተማረኩ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት ላይም ይለማመድባቸው የነበረውን የግፍ አይነት በወቅቱ ባይናቸው ያዩ የነበሩ የትግል ጓዶቹ የወዲ አፈወርቂን ድርጊት ከጀግንነት ቆጥረውት ነበር። የኢሳያስ ጓዶች ኢሳያስ በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ የፈጸመውን ግፍ በኛ ላይ ሊፈጽመው ይችላል ብለው አላሰቡም ነበር። በአንድ የተወሰነ የታሪክ ወቅት የሚከሰት የጭካኔ ድርጊት ግን ሁሌም Precedence አለው። ቶላና ጫላ አብረው ሳሉ ጫላ በበየነ ላይ የሚፈጽመውን ዘግናኝ ድርጊት ጫላ በቶላ ላይ ላለመፈጸሙ ዋስትና የለም። እንዴውም ጫላ በበየነ ላይ የፈጸመው ዘግናኝ ድርጊት በቶላ ላይ ሊፈጸመው እንደሚችል precedence አለ። ኢሳያስ አፈወርቂም በነዮሀንስና በተማረኩ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት ላይ ያደረገውን ግፍ የራሱን አገር ሲፈጥር ከሁሉ አስቀድሞ ያስቀጠለው አብረውት በነበሩ፤ ግፍ ሲፈጽም እያዩ «አበጀህ፤ ጎሽ፤ ጀግኖቻችን ነህ» ባሉት የእድሜና የትግል አጋሮቹ ላይ ነው።
በኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ አራማጆች ላይ መርዝ ከመርጨት የማይቦዝነው የኦነግ የምሁር ሊጎች ምላስም ነገ አገር ሲመሰርት ቀድሞ የሚበላው ዛሬ አጅበው «አበጃችሁ፤ ጎሽ፤ ጀግኖቻችን ናችሁ» የሚሉትን ጭፍን ደጋፊዎች ነው። እነዚህ ኦነጋውያን ኢትዮጵያዊ ብሔርተኞች ጋር በኢትዮጵያ ውስጥ አብረው እያሉ ማምጣት ያልቻሉትን ነጻነት የራሳቸውን መንግስት መስርተው ሊያመጡት አይችሉም። «የምጨቆነው ጨቋኞቹ ወገኖቻችን ስላልሆኑ ነው» በሚል ያስተሳሰብ ዝንፈት ያሰለፉት ኃይል ይህንን እውነት ያስተዋለው አይመስልም። የራሳቸውን አገር ቢመሰርቱ ጨቋኝ እንጂ ጭቆና እንደማይቀየር የተገነዘቡት አይመስልም። ጨቋኑ መሬት ነጣቂ ከሆነ የራሳቸውን አገር ቢመሰርቱ መሬት ነጣቂው ቢቀየር እንጂ መሬት ነጠቃው እንደማይቀር አላጤኑትም።
እንዴውም በሚመሰርቱት የራሳቸው አገር በንጉሱ ዘመን ከነበረውና «የማንም ንብረት ለግለሰብ ተብሎ አይነካም» ከሚለው ህገ መንግስታዊ መብት አኳያ ካየነው ደግሞ ቁልቁለቱ በጣም ቁልቁል ነው። የራሳቸውን አገር ቢመሰርቱ ገራፊ ቢቀይሩ እንጂ ግርፊያ አይቀርም። በኢትዮጵያዊ ብሔርተኞች ላይ ዛሬ መርዝ የሚተፋው የኦነጋውያን ዶክተሮች ምላስ ነገ ላይ አገር ስለመሰረቱ precedenሱ ጥሩ ሊሆን አይችልም። ኤርትራ የሆነው ኦነግ በሚፈጥረው አገር አይሆንም ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው። ኤርትራ ላይ የምናየውን ፊልም ኦነግ በሚፈጥረው አገር የማናይበት ምንም ምክንያት የለም። ለምን ቢባል የራስ መንግስት ለመመስረት የሚደረግ ትግል እንደማትጨቆን፤ እንደማትገደል፤ ንብረትህን እንደማታጣ፤ ነጻነትህን እንደማትገፈፍ ዋስትና ሊሰጥ አይችልምና ነው። በኤርትራና በደቡብ ሱዳን እንደታየው የራስ መንግስት ለመመስረት የሚደረግ ትግል ላለመጨቆን፤ ላለመገደል፤ ንብረትን ላለማጣት፤ ነጻነትህን ላለመገፈፍ ዋስትና አይሆንም።

ከዚህ በተጨማሪ የራስ መንግስት ለመመስረት የታገሉት ኤርትራውያንና ደቡብ ሱዳናውያን ለመውቀውስ የሚያዳግት ጨካኝ አገዛዝ «ተጎናጽፈዋል»። ለመውቀስ የሚያዳግት ያልሁት ስለ አንድ ነገር ነው። ኤርትራውያንና ደቡብ ሱዳናውያን በርሀ ሲወርዱ «ጭቆና እየደረሰብን ያለው ስልጣን ላይ ያለው የኔ ዘር ስላልሆነ ነው፤ የኔ መንግስት ስላልሆነ ነው» በሚል መነሻ ስለሆነ ዛሬ በትግላቸው የኔ የሚሉት መንግስት አቁመው ሲጨቁናቸው «የኔ መንግስት ጨቁኖኛል» ብለው ለመውቀስ፤ የነበራቸው ነጻነት እንዳጡ ለመናገርና ለመታገል ያሳፈራቸው ይመስላል። የራስ መንግስት ለመመስረት ያታገሏቸው ፋኖዎች ነጻነት ሊሰጧቸው እንደማይችሉ በሚጭኗቸው የጭቆና ቀንበር ውስጥ ገብተው ሲገነዘቡት ፋኖዎቹ እንደሸወዷቸው ቢገባቸውም የውሽማ ለቅሶ እያለቀሱ እንዳይነወሩ የከፋ የራስ የግፍ አገዛዝ ተሸከመው መኖርን ይመርጣሉ።
ስለዚህ የነጻነት አንኳሮች የሆኑት የንብረት መብት፣ በራስ ሀብት የማዘዝ ሙሉ መብት፣ ሀሳብን የመግለጽ መብት፣ንብረት የማፍራት መብት፣ በእኩልነት የመተዳደር መብት፣ወዘተ የራስ መንግስት ለመመስረት በሚታገሉ ቡድኖች ሊረጋገጥ አይችልም።
የራስ መንግስት ለመመስረት የሚታገሉት ፋኖዎች አላማቸው የራሳቸውን ባንዲራ ፈጥረው፤ የክብር ዘብ አሰልፈው የህይወት ዘመን ፕሬዝደንት ሆነው የሚገዘግዙት አገር ለመፍጠር እንጂ ትክክኛ የህዝብን የመናገር፣ የመወከልና የንብረት መብት ነጻነት ለማምጣት አይደለም። ለዚህ ቢሆን ኖሮ የታገሉት የየለቱ ንግግራቸውና ተግባራቸው ሁሉ በራስ ሀብት ስለማዘዝ፣ ስለመናገር፣ ስለመወከልና ስለንብረት ማፍራት መብት ነጻነት ምስክር ሆኖ ይታይ ነበር። ኦነጋውያንም የሚታገሉት ለነጻነት ቢሆን ኖሮ የተለየ አስተሳሰብ ባላቸውና በሰላ በሚሞግቷቸው የኢትዮጵያ ብሔርተኞች ላይ አይን ያወጣ ስድብ፣ ዘለፋ፣ ማዋረድ፣ ተክለ ስብዕና ገደላ፣ ጥላቻና ርኩስ መንፈስ የተሞላበት ንግግር በማራባት አይጠመዱም ነበር። ለነገሩ ነጻነት ለማምጣት የራስ መንግስት ለመመስረት መታገል አያስፈልግም። የራስ መንግስት ለመመስረት ሳትነሳ በአንድነት እየኖርህ አብረህ እስከታገልህ ድረስ ነጻነትህ ታገኛለህ። የኦነጋውያን መንፈስ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። የራሳቸውን መንግስት ለማቆም ሲሉ ከሰይጣንም ጋር ቢሆን የሚተባበሩ ይመስለኛል። ከሰይጣን መንፈስ ነጻነት ሊቀዳ አይችልም። ከሰይጣን መንፈስ የሚቀዳው ሁሉ ብሩቁ የሆነ ጨካኝ አገዛዝ ብቻ ነው።

ከፍ ብዬ በአንድነት እየኖርህ አብረህ እስከታገልህ ድረስ ነጻነትህ ታገኛለህ ብያለሁ። ይህን ስል በአንድነት ለነጻነት መታገል የራስ መንግስት መስርቶ ለነጻነት ከመታገል በብዙ እጥፍ ይቀላል ለማለት ነው። ዛሬ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ብትሆን ኖሮ 95 ሚሊዮን ህዝብ ለነጻነት አብሮ ይታገል ነበር። 95 ሚሊዮን ህዝብ ለነጻነት አብሮ ሲታገል የነጻነት ቀን ሩቅ አይሆንም። ዛሬ የራሳቸውን መንግስት የመሰረቱት ኤርትራውያን ብቻቸውን ቢታገሉ ግን ከአምስት ሚሊዮን ኤርትራውያን ግማሹ ያልህ እንኳ ለነጻነት ለመታገል መነሳቱ ያጠራጥራል። ከፍ ብዬ ኤርትራውያን ለመውቀስ የሚያዳግታቸው አገዛዝ አቁመዋል ብዬ ነበር። ዛሬ ምንም እንኳ በባርነት እየኖሩ ቢሆንም የታገሉለት አገዛዝ ስለሆነ ብቻ ግን የኢሳያስን አገዛዝ «የኛ መንግስት ነው» ብለው ተቀብለው ለመኖር የቆረጡና ለነጻነት ትግል የማይደፍሩ ቁጥራቸው የማይናቅ መሆኑ እሙን ነው። ይህንን አጥር ሰብሮ ለነጻነት ለመታገል የሚነሳው ኤርትራዊ ቁጥር ግፋ ቢል ግማሹ የኤርትራ ህዝብ ቢሆን ነው። በዚህ ስሌት መሰረት የኤርትራ ህዝብ ለነጻነት ሊታገል ቢነሳ 2.5 ሚሊዮን ኤርትራዊ ለነጻነት ሊታገል ይችላል ማለት ነው። 2.5 ሚሊዮን ኤርትራዊ በአገሩና 95 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ በአንድነት በሚያደርጉት የነጻነት ትግል መካከል ያለው የነጻነት ቀን ርዝማኔ ልዩነት ግልጽ ነው። 95 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ በአንድነት አይደለም ታግሎ ተራራ ላይ ወጥቶ ሽንቱን ቢሸና የማይቆም ናዳ ይፈጥራል። በአድነት ለነጻነት የመታገል ጥቅሙ ይህንን ያህል ጥልቅ ነው።
«እየተጨቆንን ያለነው ስልጣን ላይ ያሉት ጨቋኞች የብሄረሰባችን አባላት ስለልሆኑ ነው» በሚል የነጻነት ጥማትን የራስ መንግስት በመመስረት ለማስተንፈው መሞከር መዳረሻው እንደ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን ለነጻነት ዋስትና የማይሰጥ የራስ መንግስት ማቆም ብቻ ነው። ውጤቱም የነበረውን አንጻራዊ ነጻነት በባርነት ቀይሮ ለማማረር የሚቸግር ጨካኝ አገዛዝ ተከናንቦ የሚገኘው ነገር ጥቅም ከተባለ ብጣቂ የቴምብር ወረቀትና የራስ ባንዲራ ብቻ ነው። ትርፉም የነበረን አንጻራዊ ነጻነት መጨረሻው በማይታወቅ ባርነት መቀየር ብቻ ነው።
ስለዚህ «የምንጨቆነው ጨቋኞቹ የኛ ብሄረሰብ አባላት ስላልሆኑ ነው» በሚል ቅስቀሳ ዘረኛ ድርጅቶችን የምትከተሉ የኔ ትውልድ ወጣቶች አትሸወዱ። «የምንጨቆነው ጨቋኞቹ የኛ ብሄረሰብ አባላት ስላልሆኑ ነው» በሚል የራስ መንግስት ለመመስረት ድርጅት አቁመው እየታገሉ ያሉት የብሔረሰባችሁ አባላት የሆኑ ፖለቲከኞች ነጻነትን ሊሰጧችሁ አይችሉም። ነጻነት የሚገኘው በአንድነት በሚደረግ የነጻነት ትግል ብቻ ነው። የብሔረሰባችሁ አባላት የሆኑ ፖለቲከኞች ነጻነትን ሊሰጧችሁ ከፈለጉ አገር መመስረት ሳይነሱ በአንድነት ታግለው ሊሰጧችሁ ይቻላቸዋል። የራስ መንግስት ለመመስረት ቢነሱ ግን ግፋ ቢል የሚያቆሙላችሁ አገዛዝ እንደ ኢሳያስ አፈወርቂ አይነት መንግስት ነው። ይህም ሲደላ ነው። እንደ ሶማሊያ መሆን አለና። ስለሆነም እነሱን በጭፍን ከመከተል ከጥላቻ ወጥታችሁ ዛሬ በሌሎች ላይ እያደረጉት ያለውን ክፋት ነገ አገር ሲመሰርቱ በማይመቻቸው የብሔረሰባቸው አባል ላይም ዛሬ በሌሎች ላይ እያደረጉት ያለውን ሊያደርጉ እንደማይችሉ ዋስትና የላችሁም። የዛሬ ድርጊት የነገ precedence አለው፤ የዛሬ ድርጊት የነገን ቁልፍ ይይዛልና። በአንድነት እየኖርህ አብረህ እስከታገልህ ድረስ ነጻነትን የማታገኝበት ምንም ምክንያት የለም። የራስ መንግስት የመመስረት አባዜ የተጠናዎታቸው ዘረኛ ግለሰቦች ትናንሽ ኢሳያስ አፈወርቂዎች ብቻ ናቸው። ኢሳያስ አፈወርቂ የራስ መንግስት በመመስረትና በነጻነት መካከል አንዳች ግንኙነት እንደሌለ፤ እንዴውም ተቃራኒ እንደሆኑ ፐርፈክት የሆነ ምሳሌ ነው። አበቃሁ!

No comments:

Post a Comment