በ10.05.2016 ላይ ከመላው የኖርዌይ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች የኖርዌይ መንግስ በህገ ወጥ መንገድ 800 ኢትዮጵውያንን በሃይል ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በራሳቸው ባለስልጣን እና በራሳቸው ሚዲያ ካስነገሩ በኋላ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያሳዘነ ብሎም ያስቆጣ ነበር። ያሳዘነበት ምክንያት ኖርዌይ የራሷን ዜጎች ከአንድም ሶስት ግዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ችግር ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ስታስጠነቅቅ በዚው ግዜ ውስጥ ከ800 በላይ 60 ህጻናትን ጨምሮ ጸጥታዋ ወደተናጋው አገር እንመልሳለን በማለታቸው በአለም የሰባዊ መብት ከሚከበርባቸው ግንባር ቀደም እንደውም በአንደኝነት የምትጠቀሰው አገር በኢትዮጵያውያኖች ላይ የሰባዊ መብት ጥሰት መደረጉ አሳዝኖናል። ያስቆጣን ደግሞ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎች መብታችን ተገፎ ያለ አግባብ ለረጅም አመታት በካንፕ ማስቀመጣቸው ሳያንሳቸው በግፍ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ አሳልፈው ለአንባ ገነን መንግስት ሊሰጡን መሆኑን በሚዲያቸው መስማታችን ከዚህ ቀደም ተደርጎ የማይታወቅ ጠንከር ያለ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ቁጣችንን ለመግለጽ የችግሩ ተጠቂዎች ከያሉበት ተሰባስበው በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ በመገኘት ችግራችንን በቁጣ ለኖርዌይ ማህበረሰብ ብሎም ለአለም ህብረተሰብ እንድናሰማ አዘጋጅቶን ነበር።
ከዋናው ከተማ ኦስሎ ራቅ ካለ ቦታ የመጣን ስለነበረ ሌሊቱን ተጉዘን ጠዋት ነበር የደረስነው። ኦስሎ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያኖችም ተቀብለውን ወደተዘጋጀው ማረፊያ ቦታ በመውሰድ የሰልፉ ሰዓት እስከሚደርስ ድረስ ከ18 ያላነስን ሰዎች ከሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ እና ከኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ኮሚቴዎች ጋር ስለ ሰላማዊ ሰልፉ እና ጠንከራ ተቃውሞ ሰልፍ ስለማድረጉ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሃሳቦችን በማንሸራሸር ከተወያየን በኋላ በኖርዌይ ህግ መሰረት ጠንካራ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ከ25 ሰው በላይ መሆን አለበት ስለሚል ጠንካራ ሰልፉን ለመውሰድ ከ25 ሰው በላይ ሰው ካለ ተስማምተን ነበር። ከዚህ ስብሰባ የታዘብኩት ሁለት ነገርን ነው። የመጀመሪያው በመስማማት የተስማሙ እና ሁለተኛው ደግሞ በመስማማት ያልተስማሙ ናቸው። እነዚህ ሁለት ሃሳቦች ተይዘው ወደ ሰልፉ መነሻ ቦታ ሄድን። ሰልፉ መነሻ ቦታ ላይ የጠበቁን ሰዎች በዛ ያሉ ነበሩ በግምት በመቶ የሚቆጠሩ ነበሩ። የዚን ግዜ በልቤ ውስጥ ከዚህ በፊት ተደርጎ የማይታወቀው ጠንካራው ሰላማዊ ሰልፍ ከበቂ በላይ ስለሆንን በኢትዮጵያ ያለውን ችግር እና የኛንም ችግር ለኖርዌይ ህዝብም ለአለምም ህብረተሰብ የምናሳውቅበት ግዜ በመሆኑ ልቤን ደስታ ሞልቶት ነበረ።
ሰልፉ ተጀመረ በተለያዩ ወንድሞች እና እህቶች ማይክሮፎኑን በመያዝ የተቃውሞ መፈክሮችን እያሰማን በከተማው መሃል መንገድ ጀመርን ። የተቃውሞ ድምጻችንን እያሰማን ጥቂት የማይባል ጉዞ ከተጓዝን በኋላ የኖርዌጃን ሚዲያ TV2 የሚባለው መስራቤት ደረስን እዚህ ጋር ሁላችንንም እንድንቆም በማስደረግ ብዙ አመት ኖርዌይ የኖረ ኢትዮጵያዊ ወንድማችን ለግዜው ስሙን መግለጽ አይጠበቅብኝም የድምጽ ማጉያውን በመያዝ የሁሉንም ሰልፈኛ ስሜት በሚነካ መልኩ የኖርዌጃንን ሚዲያ መውቀስ ጀመረ ።《የኢትዮጵያን እውነተኛ ገጽታ ታውቃላችሁ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል ታውቃላችሁ በኢትዮጵያን ላይ የሚደርሰውን እስራትና ሞታ ታውቃላችሁ ነገር ግን ይሄንን እያወቃችሁ እውነታውን ህዝባችሁ እንዲያውቀው አላደረጋችሁም TV2 በናንተ አፈርን》 በማለት በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሰልፈኛ ልቦናውስጥ ያለውን ሃሳብ ስሜት በሚነካ መልኩ ኢትዮጵያውስ ያለውን ችግር ዘርዝሮ በመንገር የኖርዌጃን ጋዜጠኞች ግን እውነታውን እያወቁ ለህዝባቸው በመደበቃቸው ከፍተኛ ትችት እና ወቀሳ በማስተላለፍ ሰልፈኛው ድምጻችን እስከሚዘጋ ድረስ ያስጮሀ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ብየዋለው። ይሄንን ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ ሳላደንቀው እና ሳላመሰግነው ማለፍ አልፈልግም በእውነት ላይ የቆምህ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ልጅ ምስጋናዬ ይድረስህ ብያለው።
ሰልፉ ወደፊት መጓዝ ጀመረ ሁለት ፈረስ ላይ የተቀመጡ ፖሊሶች ከፊታችን ሰልፉን ይመሩታል ሁለት የፖሊስ መኪና ከፈረሶቹ ፊት አሉ የፖሊስ ልብስ ያለበሱ ፖሊሶች በርቀት ይከተሉናል። ጠንካራ ሰልፍ እንደሚደረግ መረጃው የደረሳቸው ይመስሉ ነበር ሁኔታቸውን ለተመለከተ… እኛ ውስጣችን ተናዷል ኖርዌይ በኢትዮጵያ ስደተኛ ላይ ያላት አመለካከት ጤናማ አይደለምና። ሰልፉ ቀጥሏል የሰልፉ መጨረሻ ፍትህ ሚንስቴር በር ላይ ነበረ።
ከተማውን በተቃውሞ ድምጽ እያናወጠነው ወደ ፍትህ ሚንስቴር ህንጻ አመራን እዛም እንደደረስን ያ ጀግና ወንድማችን በድጋሚ ማይክራፎኑን ያዘው የኖርዌይ መንግስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለ አግባብ በመደገፋቸው ህዝባችን ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል የኖርዌይ መንግስ በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ እንደሆነ ይነግራቸው ጀመር። የቃላት አመራረጡ የድምጽ አወጣጡ ሰልፈኛውን ብቻ ሳይሆን የፍትህ ሚንስቴር በር የሚጠብቁትን ፖሊሶች እና አጅበውን የመጡትን ፖሊሶች ጭምር ቀልብ የገዛ ነበር። እውነት ለመናገር ሁሉም ኢትዮጵያ ቆርጦ ቢታገል ትግሉ ትልቅ ደረጃ ላይ አድርሶ በአንድ ማስተሳሰር በተቻለ ነበር። በመጨረሻም ከፍትህ ሚንስተር መስሪያ ቤት በመውጣት ሰልፈኞችን አነጋግራለች። ስለ ሰልፋችን አላማ ከሚንስተር መስራቤት ለመጡት ገለጻ ከተደረገላት በኋላ ስለ ሰልፉ አላማ የሚነግር ደብዳቤ ከተሰጣት በኋላ እሷም ደብዳቤውን ከተቀበለች በኋላ ለሰልፈኞቹ ንግግር አድርጋለች።
ከሚንስተር መስራቤት የመጡት ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሰልፈኞቹ ወደ ተባለው ጠንካራ ሰልፍ ለመሄድ እየተነጋገርን እያለ ድንገት አንድ ሰው አዲስ ሃሳብ ይዞ ብቅ አለ የሰልፉን አዘጋጆችን በመለየት ጠንካራ ሰልፍ የተባለውን ማድረግ እንደሌለባቸው ይነግራቸው ጀመር። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ትልቅ የፖለቲካ ስራ ከኖርዌጃን ባለስልጣናት ጋር እየተሰራ እንደሆነ እና ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለ በማሳወቅ ዛሬ ጠንካራ ሰልፍ ቢደረግ እና ከፖሊሶች ጋር ብትጋጩ የተጀመረው ስራ እንደሚበላሽባቸው በመግለጽ የታሰበው እና ከሁለት ወር በላይ የተዘጋጀንበት ሃሳብ በማስለወጥ ሊወሰድ የታሰበውን ጠንካራ ሰልፉን አስቀርቶታል። ሲጠቀልለው ከኖርዌይ ባለስልጣን ጋር የተጀመረው ውይይት ካልተሳካ ግን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በድጋሚ በመቀስቀስ ጠንካራ ሰልፉን እንደሚወሰድ አሳውቋል። ለዚህም አላፊነቱን እንደሚወስድ በመናገር የሰልፉን ድምዳሜ ነግሮ ሰልፉ ተጠናቋል።
እኛም ውሳኔውን በመጠባበቅ ላይ ነን ያለውን ሁኔታም እየተከታተልኩኝ ለሚዲያ ለማቅረብ እሞክራለው።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚሰራው ስራ ሃላፊነትን በመውሰድ ተጠያቂነት እንዲኖርበት ያስፈልጋል። መልካም የሰራ ክብር ልንሰጠው እንደሚገባ ሁሉ ስህተት የሰራም ስህተቱ በአደባባይ ሊነገረው ይገባል እላለው። ለጊዜው አበቃው።
No comments:
Post a Comment