Saturday, May 14, 2016

‹‹ሲደበድቡኝም አንተ አማራ፣ አንተ ትምክተኛ… እያሉ ነው፤ በአማራነቴ ሲደበድቡኝና ሲሰድቡኝ እኔ ለእነርሱ አዝን ነበር›› አቶ ዘመነ ምሕረት

Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች | 
  • 0
     
    Share
ጥያቄ፡ መቼና እንዴት ወደፖለቲካ እንደገቡ፤ በፖለቲካ ውስጥ ለስንት ጊዜ እንደቆዩ ቢገልጹልን?
ዘመነ ምሕረት፡ ቀጥታ ወደ ፖለቲካ የገባሁት በ1997 ዓ.ም. በቅንጅት ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን በቀጥታ ባይሆንም የፖለቲካ ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ ከ91 ዓ.ም. ከአገዛዙ ጋር በኢትዮጵያዊነት ላይና ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጋር ተያይዞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርር ቤት ተማሪ በነበርኩ ጊዜ ያሳድዱኝ ነበር፡፡ ፈጽሞ ተግባብተን አናውቅም፡፡ በ1993 ዓ.ም በነበረው የአዲስ አበባና በሌሎች ዩንቨርሲቲዎች በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ እኔ ጎንደር ነበር፤ ሆኖም በቀጥታ እሳተፍ ነበር፡፡ ሆኖም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆንኩት በ1997 ዓ.ም. የመለው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን በመቀላቀል ነበር፤ ወዲያው ቅንጅት ሲመሠረት ወደ ቅንጅት አብረን ገባን፡

13241299_1209752182382726_681976981679470613_nየፖለቲካ ፓርቲ አባል እንድሆን የአሳደጉኝ ቤተሰቦች አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ አያቶቼ አርበኞች ነበሩ፡፡ ሕጻን እያለሁ ቤት ውስጥ የሚወራው ሁሉ ስለአርበኞች ነበር፡፡ የምንወረው ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያዊነትና የነገሥታቱን የእነ አጼ ቴዎድሮስን፣ ምኒልክን ብሎም የአርበኞችን ወሬ ነበር፡፡ የታሪክ መምህርም የሆንኩት በዚሁ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የአኔ ቤተሰቦች በደርግ ብዙ በደል ደርሶባቸዋል፡፡ ይሁን እንጅ እነርሱ በጊዜው ይሉት የነበረው ‹ከእንግዲህ የሚመጣው መንግሥት (በገጠር ተሓት ነበር የሚሉት) ኢትዮጵያን የሚቆራርስ፣ አገር የሚያፈርስ የትግሬ መንግሥት ነው› እያሉ ይነግሩን ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ከሕጻንነቴ ዘመን አንስቶ ምንም ዓይነት ኢሕአዴጋዊ ባሕሪ የለኝም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የፖለቲካ ትግልን ተቀላቅያለሁ፡፡
ጥያቄ፡ በፖለቲካ ተሳትፎዎ የገጠመዎ ችግር ምንድነው?
ዘመነ ምሕረት፡
በፖለቲካ ትግል ብዙ ችግሮች ደርሰውብኛል፡፡ ለአብነት ያክል እንኳን ሌሊት ቤቴ የማላውቃቸው ሰዎች መጥተው በ1997 ዓ.ም. በጥይት ተስቻለሁ፤ በሰሜን ጎንደር አለፋ ጣቁሳ ወረዳ ነው በጥይት የተሳትኩት፡፡ ደኅንቶች በተለያየ ጊዜ ያሳድዱኝ ነበር፤ ተደጋጋሚም ተክስሻለሁ፡፡ ከሥራ ሁሉ ታግጄ ነበር፤ ስብሰባ ላይ እንዳልሳተፍ ተክልክያለሁ፡፡ በሙያየ የማደግ መብት ተከልክያለሁ፡፡ ከመምህርነት በግዴታ አስወጥተው የቢሮ ሥራ ላይ መድበውኝም ነበር፡፡ እኔ የተማርኩት ታሪክ ነው፤ ነገር ግን እነርሱ የጂአይ ኤስ ባለሙያ አድርገው መደቡኝ፡፡ እንኳን እኔ በእኔ የተነሳ ብዙ ጓደኞቼና ዘመዶቼ ከሥራ ታግደዋል፡፡ በመምህራን ማኅበር ጊዜ ራሱ ብዙ ሰዎች ነው ከሥራ የተባረሩት ከእኔ ጋር ይገናኛሉ ተብለው፡፡

የሚገርምህ ሰዎቹ የኢሕአዴግ አባል ናቸው፤ ነገር ግን ከዘመነ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ቁረጡ ተብለው ነው የተባረሩት፡፡ ለምሳሌ ሙሌ ፍስሃ የማክሰኝት ርእሰ መምህር፣ አቶ አማው እባቡ የጎንደር ዙሪያ መምህራን ማኅበር ሰብሳቢ፣ ይታየው ገበያው የጎንደር ዙሪያ ሱፐርቫይዘር፣ በለጠ ታከለ የሚባል የማክሰኝት ምክትል ርእሰ መምህርና ሌሎች ብዙ ሰዎችም ከእኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው ከሥራ ወይ ይባረራሉ ወይም ደግሞ ደረጃቸው ዝቅ ብሎ እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ ብዙ ሰዎች የኢሕአዴግ ባለሥልጣን ቢሆኑ በራሱ ከመባረር አይድኑም ነበር፡፡ ይህን ሁሉ የሚያደርገው አንድ የብአዴን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ደሳለኝ አስራደ የሚባል ሰው ነው፡፡ አሁንም ድረስ ብዙዎች እየተሳደዱ ነው፡፡
ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በፍርሃት ነው፡፡ እርሱ ሌሎችን ሰዎች ስለሚያደራጅ እንዲሁም በዙሪያው ሰው እንዳይቀርበው ካደረግን በፍርሃት ወደ እኛ ይመጣል ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡

ጥያቄ፡ በቅርቡ ታስረው ከፍተኛ የሆነ ቶርቸር እንደተፈጸመብዎ ተገልጿል፡፡ ስለተፈጸመብዎ ነገር በዝርዝር ያጫውቱን?
ዘመነ ምሕረት፡
ጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ማክሰኝት የጽዮን ማርያም ታቦትን ወደ ጥምቀተ ባሕር ስናወርድ በኋላየ የማላውቃቸው ሰዎች መጥተው ያዙኝ፡፡ ሲይዙኝ ምንድን ነው ብየ ገጠምኳቸው፡፡ ከያዙኝ ሰዎች ጋር ስንተናነቅ ፌደራል ፖሊስ ወረረኝ፡፡ የፌደራል ፖሊሶች ከስድስት መኪና በላይ ይሆናሉ፡፡ መጥተው ከዚያው ላይ በአፈ ሙዝ ደበደቡኝ፡፡ ዕውነት ለመናገር መጀመሪያ ሲይዙኝ የሆነ ከቤተሰብ ጋር እኔ ሳላውቀው በተፈጠረ ችግር ሊይዙኝ የመጡ ወንበዴዎች ናቸው የመሠሉኝ እንጅ በመንግሥት የተላኩ እንደሆኑ አላወቅኩም ነበር፡፡ የፖሊስ ዩኒፎርም አልለበሱም፤ ሲቪሎች ናቸው፡፡ ወታደሮቹ ከሕዝብ ፊት ደበደቡኝ፡፡ ልጄና ሚስቴ አብረውኝ ነበሩ፡፡ ልጄ ሕጻን ነው እኔን ሲደበድቡኝ እያለቀሰ መጣ፡፡ የሚገርምህ ልጄን በአፈሙዝ ደበደቡት፡፡ የቀበርከውን አምጣ፣ መሣሪያህን አምጣ አሉኝ፡፡ ቤቴን ሲፈትሹ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ የሰበሰብኩትን የአዲስ ራዕይ መጽሔት አገኙ፡፡ ምክንያቱም በየወሩ የሚሉትን ለማየት ስበስበው ነበር፡፡ በኋላ የደበቅኩት ቦንብ እርሱ ነው አልኳቸው፡፡ የተለያዩ የፖለቲካና የታሪክ መጽሐፍት እንዳገኙ አሁንም ከልጄም ከሚስቴም ፊት ደበደቡኝ፡፡ ሚስቴ ከፊት አትምቱት ብላ እየጮኸች ወጣች፡፡ ጫማዬን አስወልቀው ካሰሩኝ ወደ መኪና ሲወረውሩኝ ሦስት ዓመት የሚሆነው ልጄ መጥቶ ሲይዘኝ መጥቶ ሲይዘኝ በአፈሙዝ መቱት፡፡ ከዚያ ወደ ጉማራ ወንዝ ስንደርስ ዓይኔን ሸፈኑኝ፤ ከዚያ በኋላ የት እንዳስገቡኝ አላውቅም፡፡ አዘዞ ተክለ ሃይማኖት አካባቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ መጀመሪያ የያዘኝ ሰው አሸናፊ ተስፋው የሚባል ነው፤ ከዚያ በኋላ ግን አላውቃቸውም፤ ትግሬዎች ናቸው፡፡ ትግርኛ ቋንቋ ተናገር፤ አንተ ትምክተኛ፣ ነፍጠኛ፣ የአማራን የበላይነት ለማምጣት የምትጥር፣… ብዙ ብዙ ነገር ነው የሚሰድቡኝ፡፡ የዱላው ነገር ቅጥ የለውም፡፡ ከአውሬም አይጠበቅ እንኳን ከሰው፡፡ እኔን በጣም ደብድበውኛል፤ የኔ ሳይሆን ልጄ ላይ የሠሩት ነው የሚያሳዝነኝ፡፡ እኔማ መቼም አንድ ጊዜ የፖለቲካ ተሳትፎ አድርጌያለሁ፡፡ ወንጀል ባይሆንም ተቃውሚያለሁ፤ አምኜበትም ነው የገባሁ፡፡ ልጄ ግን ምንም ሳይሠራ መደብደቡ ያሳዝነኛል፡፡
ወያኔዎቹ ከአማራው ላይ ያላቸው ጥላቻ በጣም ከፍተኛ ነው ብልህ አልገልጸውም፤ በጣም በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ሕወሓቶች በተቃዋሚ ላይ ሳይሆን በአማራ ላይ ጥላቻ እንዳላቸው ነው የተገነዘብኩት፡፡ ሲደበድቡኝም አንተ አማራ፣ አንተ ትምክተኛ… እያሉ ነው፡፡ ስታያቸው ጥላቻቸው ከፍተኛ በሽታ የሆነባቸው ይመስለኛል፡፡ በአማራነቴ ሲደበድቡኝና ሲሰድቡኝ እኔ ለእነርሱ አዝን ነበር፡፡ የሚናገሩት ቋንቋ ከሰው የማይጠበቅ የአውሬ ልትለው ትችላለህ፡፡ አማራ ሆኖ መወለድ ወንጀል ነው ለእነርሱ፤ አማራ ምን እንዳደረጋቸው አንተ ንገረኝ፣ ሌላም ሰው ካለ ቢያስረዳኝ ደስ ይለኛል፤ የታሪክ መረጃም ባገኝ ደስ ባለኝ፤ ያሳዝናል፡፡ ከሚደበድቡኝ ይልቅ አነጋገራቸው ነው የሚያመኝ ለእኔ፡፡ ዱላቸውማ ማንንም በተለይ አማራ ሁሉ እንደሚደበድቡት ነው የደበደቡኝ፡፡ አነጋገራቸው ከጤነኛ ሰው ሳይሆን አእምሮው ከታወከ ሰው እንኳ የማይጠበቅ ነው፡፡
ጉድጓድ ውስጥ ራቁቴን ከተው ይሸኑብኛል፤ ይተፉብኛል፤ ትግርኛ ቋንቋ ተናገር ይሉኝ ነበር፡፡ ሱሪየን ፓንቴን ሁሉ ጨምሮ አስወልቀውኛል፡፡ ከላየ ላይ ከሸሚዜ ውጭ አልነበረም፡፡ ዓይኔ ተሸፍኖ ስለነበር የሚደበድቡኝን ሰዎች አላውቃቸውም፡፡ የምሰማው ስድባቸውን ብቻ ነው፡፡ ከፈለጉ ደግሞ አንስተው ሰቅለው እያገላበጡ ይደበድቡኛል፡፡ ያሳዝናል፤ ሁሉንም ለመናገር ቃላት የለኝም፤ አልችልምም፡፡ በጠቅላላው ደስ የማይል ነገር ነው፡፡
ወደ አዲስ አበባ ሲያመጡኝ ወዴት እየወሰዱኝ እንደሆነ አላወቅኩም ነበር፡፡ ማርቆስ ስደርስ ዓይኔን ገለጡልኝ፡፡ የመኢአድ አባል የሆነው መለሰ መንገሻን ማሰራቸውን አላወቅኩም ነበር፡፡ በድብደባ ብዛት ሁለታችንም ራሳችን ስተን ነበር፡፡ ዓይናችን ማርቆስ ላይ የተሸፈነውን አንስተውልን ማርቆስ ካለፍን በኋላ ሽንት እንድንሸና ከመኪና ወረድን ወረድን፡፡ ከዚያ መለሰ መንገሻ መሆኑን በዓይኑ ለየሁት እንጅ የሁለታችንም ሰውነት በድብደባ ብዛት ተለዋውጠን ስለነበር ማን ማን መሆናችን ራሱ አይለይም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ስንገባ ጨለማ ቤት ውስጥ ቢሆንም ከሰው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተጨመርን፡፡

የተያዝንበት ምክንያት ከፓርቲው እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እነርሱ ሲጠይቁኝ የነበረው ለምን ከአቶ አበባው መሐሪ ጋር አብረህ አትሠራም? የመኢአድ አመራር ሆኖ ከአንተ ጋር አብረው የሚሠራውን ሰው ንገረን፡፡ ያደረጀውን ሰው ንገረን፡፡ ለምን አርፈህ አትቀመጥም? የአማራ የበላይነትን ልታመጣነው የምትታገለው የሚሉ ነገሮችን ነው የጠየቁኝ፡፡ ከግንቦት ሰባት ጋር ትገናኛለህ ምናም የሚሉትን ለስሙ ነው የሚጠይቁኝ፡፡ ወዲያውኑ ከአማራ ጋር አያይዘው ነው የሚወርዱብኝ፡፡ ማጠንጠኛቸው ዞረው ዞረው ከአማራ ጋር ነው የሚያይዙት፡፡
በማዕካላዊም በቃሊቲም ከ14 ሕፃናት እስከ 70 ዓመት የሚሆናቸው አዛውንት አማሮች ታስረዋል፡፡ ከእኔ ላይ የደረሰው ድብደባና ማሰቃየት ከሕፃናትም ከሽማግሌዎችም ላይ ደርሷል፡፡ ልዩነት የለውም፡፡ በደረጃ ባስቀምጥልህ በዓይኔ እንዳየሁት እንደ አበበ ካሴ የተጎዳ የለም፡፡ አበበ ካሴ አሁን ሰባት ዓመት ተፈርዶበት ዝዋይ ነው፡፡ እሱን ጓያ የሰበረው አስመስለው ሽባ ሆኖ ነው እየሔደ ያለው፤ አካሉ ስንኩል ሆኗል፡፡ እንደነገረኝ ከሆነ መውለድም ከዚህ በኋላ አይችልም፡፡ አበበ አካሉ የተባለው የመኢአድ አባልም በድደባ እጁ ሽባ ሆኗል፡፡ ሦስተኛ እንደ ጌትነት ደርሶ፣ መቶ አለቃ ጌታቸውና ቢሆን አለነ ዓይነት ድብደባና ቶርቸር የደረሰሰበት ሰው የለም፡፡ የአግበው ሰጠኝ፣ የመለሰና የእኔ ተመሳሳይ ነው፡፡ የእኔን ድብደባና ቶርቸር ከእነርሱ ጋር አላወዳድረውም፡፡ የእነርሱ ፈታኝ ነው፤ ይከብዳል፡፡
በተለይ ሲመረምሩህ ብሔርህ ማን ነው? ሲሉህ አማራ ነው ካሉህ ጥላቻቸው ይበረታል፤ በጣም ይገናል፡፡ ከዱላቸው ፊታቸው ያስፈራል፡፡ በጣም የተለየ ያደርጉታል፡፡ ገምናናው ጨቅሌ የሚባል የ14 ዓመት ልጅ ከቤተሰቦቹ ጋር ተጣልቶ ከአጎቱ ልጅ ጋር የቀን ሥራ ለመሥራት ሲሔድ ዳንሻ ላይ ያዙት፡፡ ታጥቀህ ኹመራን ልታስመልስ ነው ብለው ነው የደበደቡት፡፡ እዚያ አካባቢ አማራዎች ከተያዙ የሚያገናኙት ከወልቃይትና ጠገዴ ድንበር ጋር ነው፤ ከሥልጣናቸው ጋር ነው የሚያገናኙት፡፡
አስበው ሕፃን ነው፤ ከፍተኛ ድብደባ ደብድበውት አእምሮው ተጎድቷል፡፡ ሲተኛ ይቃዥ ነበር፡፡ እኔና በላይነህ ከመካከላችን እየተኛ ‹‹መጡብኝ!›› እያለ ሲባባ እንደግም ነበር፡፡ አስበው ይህ ልጅ ጭልጋ አካባቢ የገበሬ ልጅ ነው፡፡ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ በአእምሮው ገና ልጅ ነው፡፡ የራሳቸውን መሬት ቀምተው እነርሱ ኢንቨስተር ሆነው፤ ከእነርሱ በቀን ሥራ ለመሥራት ሲሔዱ አንተ ኤርትራ ልትሔድ ነው ተብለው ነው የሚደበደቡት፡፡ እትብታቸው በተቀበረበት መሬት ላይ ነው አማሮች ግፍ የሚቀምሱት፡፡

ጥያቄ፡ እንዴት ተፈተ? አሁንስ ሕይወትዎ አስተማማኝ ነው ወይ?
ዘመነ ምሕረት፡
አሁን ካለሁበት በእርግጥ እስሩ ይሻለኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም ክትትሉ ቤተሰቦቼም እኔም ላይ በጣም ከባድ ነው፡፡ ሕይወቴ አሁን የበለጠ አደጋ ላይ እንዳለ አምናለሁ፡፡ የተፈታሁት አቃቢ ሕግ አስተማማኝ ማስረጃ ማቅረብ ስላልቻለ ነው፡፡ ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ከሽብር አውጥቶ ወደ ወንጀል ክስ ቀየረው፡፡ ስለዚህ በወንጀል ሕጉ መሠረት ነው በዋስትና የወጣሁት፡፡ ገና ዋስትና ተሰጠኝ እንጅ ነጻ ነህ አልተባልኩም፡፡
ከሥራ ታግጃለሁ (ደብዳቤውን እያሳየ)፡፡ ባለቤቴ መምህር ናት በእርሷ ደመወዝ ነው ቤተሰብ የምናስተዳድር፡፡ ከሥራየ ያታገድኩት ደግሞ በሽብር ወንጀል የተከሰስክ በመሆኑ ነው የሚለው፡፡ እና ከሥራ አንቀበልህም ብለው አባረሩኝ፡፡ በካፌ ብቀመጥ፣ ገጠር ብሔድ ከጎኔ የማይከተሉኝ ጊዜ የለም፡፡

ጥያቄ፡ በትግሉ ይቀጥላሉ?
ዘመነ ምሕረት፡
አዎ በእርግጠኛነት በትግሉ እቀጥላለሁ፡፡ ምንም ጥርጣሬ አይግባህ፡፡ የትግላችን ሁኔታ በጣም ጠንካራ ጓዶቻችን አሉ እና እነርሱ ጋር ሆነን ውሳኔ ላይ እንደርሳለን፡፡ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክረን እንቀጥላለን፤ በኮረኮሙን ቁጥር ካላማችን የምንሸሽ ሰዎች አይደለንም፡፡ ከእነ አቶ ማሙሸት አማረና አቶ አብርሐም ጌጡ ጋር ተማክረን ወደፊት እንቀጥላለን፡፡ የመንፈስና የጽናት አባታችን ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ካስቀመጡልን የትግል መስመር ፈቀቅ አንልም፡፡

No comments:

Post a Comment