(ዘ-ሐበሻ) በሕወሓት ክፍፍል ወቅት ስልጣናቸውን እንዲያጡ የተደረጉት የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት ደርግን ለመጣል ለተደረገው ትግል ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ኦነግ፣ ሲነግና ወዘተ አስተውጽኦ እንደነበራቸው ተናገሩ:: ጄነራሉ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ግንቦት 20ን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር ስለአሰብ ወደብ ጉዳይም ተናግረዋል::
“ድሮም ቢሆን የኤርትራን ነፃነት ተቀብለው የአሰብ ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች ነበሩ። እንደነ አቶ ተወልደ ወልደ ማርያም፣ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳኤ፣ አቶ ስየ አብርሃ፣ አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ እኔም ጥያቄዎች የምናነሳበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዝርዝር ባንወያይበትም። አሜሪካ ሄጄ ሁለተኛ ዲግሪዬን ስሠራ ግን በዚህ ላይ ጥናት አካሂጄ የባህር በር መብታችንን በሕጋዊ መንገድ ማስመለስ እንደምችል የሚያረጋግጥ ድምዳሜ ላይ ደረስኩ። ባለማወቅና በመታበይ (Ignorance and arrogance) ያጣነው መብት ነው፡፡ አሁንም ግን ሕጋዊ መሠረት አለን፡፡”
ያሉት ጀነራሉ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::
አሁን እየተነሱ ባሉት የህዝብ እንስቅቃሴዎች ዙሪያ ከሪፖርተር:-
“ሕዝባዊ አመፅ እየታየ ያለው በተካሄደው ምርጫ ገዢው ፓርቲ መቶ በመቶ ማሸነፉን በገለጸበት ማግሥት ነው፡፡ ይህን ያህል የሕዝብ ተቃውሞ መነሳቱ በምርጫ ሒደቱ ላይ ጥያቄ አያስነሳም?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሜጀር ጀነራል አበበ ” የመንግሥትና የፓርቲ መዋቅሮች መደባለቅ አንዱ ትልቅ ችግር ነው። ኢሕአዴግ የመንግሥት ሚድያ፣ የመንግሥት ቢሮ፣ ገንዘብና አሉ የሚባሉ እርከኖችን ለፓርቲ ሥራ ስለሚያውል የፉክክር ሜዳው ዴሞክራሲን የሚያስችል (democracy enabling) እንዳይሆን አድርጎታል። ቻርለስ ቲሊ የሚባል ታላቅ የፖለቲካ ሳይንቲስት አንድ ፓርቲ ከሰባ አምስት በመቶ በላይ የፓርላማ መቀመጫዎችን ለብቻው ከያዘ ገና ከወዲሁ ዴሞክራሲያዊና ፍትሓዊ ያልሆነ፣ በሕዝብ ተቀባይነት የሌለው ምርጫ ነው ማለት ይቻላል ይላል። ምክንያቱም አንድ ሕዝብ ከፋብሪካ እንደሚወጣ ወጥ ምርት አይደለም። የተለያየ ፍላጎት፣ ምርጫና ዝንባሌ ስለሚኖረው። አሥር በመቶ እንኳ ተቃዋሚዎች ቢያሸንፉ መሬት ላይ ያለውን ሀቅ አያንፀባርቅም። የፌዴራሊዝም ባለሙያዎችና አገራዊ የውክልና ተቋማት ሕዝቡ ውስጥ ያሉ ልዩነቶችን ማንፀባረቅ አለባቸው ይላሉ። ስለዚህ ኢሕአዴግ አሽነፍኩ ያለበት ሒደትም የታወጀው ውጤትም አስቂኝ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ጭምር ነው። ውጤቱ ሲነገር ስቀን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ አደጋው ፈጦ እያየነው ነው። ኢሕአዴግ ማሸነፍ አይችልም ነበር እያልኩ አይደለም፡፡”
ብለዋል::
ቃለምልልሱን እንደወረደ ለግንዛቤ እንዲረዳዎ እንደሚከተለው አቅርበነዋል:-
ሪፖርተር፡- መድበለ ፓርቲ ሥርዓትና ተቋማዊ አሠራር ከመገንባት አንፃር አሁን መሬት ላይ ያለው አሠራር ከሕገ መንግሥቱ ጋር ሲታይ ምንይመስላል?
ጄኔራል አበበ፡- በጣም ዘመናዊ ሕገ መንግሥት አለን። ሕገ መንግሥቱ ግሎባላይዜሽን፣ የሌሎች አገሮች ተሞክሮና የራሳችን ሁኔታ ታሳቢ አድርጎ የወጣ ነው። ነገር ግን ፍፁም ነው ማለት አይደለም። በመሠረቱ ሲታይ ግን ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍላጎትን ያሟላ ነው። መስተካከል ያለበት ነገርም ሊኖር ይችላል። አሁን ትልቁ ችግር ያለው በተግባር ማዋል ላይ ነው። የሕገ መንግሥት ተቋማት ነፃነት የተጠበቀ አይደለም። በእኔ ግምገማ ሁሉንም ሥልጣን የያዘው አስፈጻሚው አካል ነው። የተወካዮች ምክር ቤት ከሚጠበቀው አንፃር ሲታይ ብዙ መሠረታዊ ችግሮች አሉበት። በሕገ መንግሥቱ የበላይ አካል ተቆጣጣሪ ሆኖ እያለ በተግባር ግን ሥራ አስፈጻሚ የሚያዘውን የሚፈጽም ነው፡፡ በተመሳሳይ ፍርድ ቤትም እንደዚያው ነው። በተለይ መንግሥትና ፓርቲ አንድ የሆኑበት አሠራር ነው ያለው። መለያየት አለበት። ይህ በጠቅላላ ሕገ መንግሥቱን የሚንድ አሠራር ነው። ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ህልውናም ትልቅ አደጋ ነው። ኢሕአዴግ መንግሥት በመያዙ ለአደጋው ዋና ድርሻ ቢኖረውም በአጠቃላይ ሲታይ ግን አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎችም ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው ናቸው። ሕገ መንግሥትን መሠረት አድርገው፣ በሕገ መንግሥቱ ያሉት ተቋማትን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ክፍተት ይታያል። አሁን ያለው መንግሥት ‹‹ከእኔ በላይ ማን አለ?›› የሚል እብሪትም ያለበት መንግሥት ነው። የዴሞክራሲ ምኅዳር እያጠበበ እያጠበበ ሄዷል። ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እየተገደበ ነው ያለው። አሁን ያሉትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደ ፀጋ አያይም፡፡ ኢሕአዴግ የተደራጀ የሕዝብ እንቅስቃሴ ሥጋት ይሆንበታል። ስለዚህ ፓርቲዎችን የማዳከም ሥራ ነው የሚሠራው። ይህም ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አደጋ ነው።
ከተቋማት አኳያ ሲታይም በተለይ ፖለቲካዊ ተቋማት እንደ ፓርላማ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጠንካራ ናቸው ለማለት የሚከብድ ነው። ተቋማቱ ያረጁ ናቸው። ይኼ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትና ለዴሞክራሲ አደገኛ ነው። ስለዚህ ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎችን እንደ ፀጋ ዓይቶ አብሮ የሚሠራበትንና ተቃዋሚዎች የሚጠናከሩበትን ሁኔታ መፍጠር አለበት። የፕሬስ መብትን ማረጋገጥም አለበት፡፡ በተለይ የተደራጀ ሕዝብ ተቃውሞ በሚያሰማበት ጊዜ ይህን እንደ ትልቅ ሀብት ዓይቶ መደገፍና ሕዝቡን ሰምቶ የሕዝቡን ፍላጎት በተሻለ ለሟሟላት መንቀሳቀስ አለበት። አሁን የስኳር ኮርፖሬሽንን ስናየው 77 ቢሊዮን ብር ያህል የሚያንቀሳቅስና በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ድርጅት ነው፡፡ እንዴት ነው አንድ ትልቅ በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራን ድርጅት ማን ነው የሚያስፈራራው? እነዚህ ሰዎችስ ማን ናቸው? በስኳር ያለው ችግርም በሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ እንዳለ ባለሙያዎች መረጃ አላቸው። ለምሳሌ ግልገል ጊቤ ሦስት እስከ አሁን ለምን ተጓተተ? የሥራው ጥራትስ ምን ያህል ነው? አሁን የምንፈልገውን ኃይልስ አግኝተናል ወይ? በህዳሴ ግድብ ላይም ቢሆን ብዙ ባለሙያዎች ጥያቄዎችና ሥጋቶች ያነሳሉ።
ሪፖርተር፡- የትጥቅ ትግል ከማካሄድና ሲቪል መንግሥት ሆኖ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመገንባት የቱ ይከብዳል ይላሉ?
ጄኔራል አበበ፡- የትጥቅ ትግል የፀረ ዴሞክራሲ ዘበኛን ለማስወገድ የሚካሄድ ትግል ነው፡፡ ስለዚህ የትጥቅ ትግል በኃይል የሚደረግ በመሆኑ በባህሪው ከዴሞክራሲ ጋር ግጭት ሊኖረው ይችላል። ምክንያቱም ማስገደድ ይኖረዋል። ይህ የፀረ ዴሞክራሲ ዘበኛ በሕዝባችን ትግል ከተወገደ በኋላ በሽግግር መንግሥት ቻርተርና ቀጥሎ በመጣው ሕገ መንግሥት በኩል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መንደርደርያ የሚሆን ሥራ ተሠርቷል። በዚህም የሕዝቦች መሠረታዊ ጥያቄ ለመፍታት ትልቅ ሥራ የተሠራ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ያልተሻገርናቸው ፈተናዎች አሉ። በመጀመርያ ኢሕአዴግ ራሱን መቀየር ነበረበት። የትጥቅ ትግል አስተሳሰብና የአገር ግንባታ አስተሳሰቦች መሠረታዊ ልዩነት አላቸው። ኢሕአዴግ ራሱን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ግብዓት ከሆኑ እሳቤዎች ጋር አጣጥሞ የሄደ አይመስለኝም። ኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የእኛ ትውልድ የአማፂ ትውልድ ነው። የአማፂ ትውልድ የዴሞክራሲ ትውልድ መሆን አይችልም። ስለዚህም ሌሎች ፓርቲዎችም ራሳቸውን በሕገ መንግሥቱና በዓለም ላይ ካሉ ዘመናዊ እሳቤዎች ጋር ማጣጣም ይኖርባቸዋል። የእኛ ትውልድ ከራሱ እሳቤና ተግባር ውጪ ያለን አካል መብት የማያከብር ‹‹እኔ ብቻ ነኝ ልክ›› የሚል አክራሪነት የሚታይበት ትውልድ ነው። ተማሪ ሆነን ሰላማዊ ሠልፍ እንውጣ በምንልበት ጊዜ እምቢ የሚል ተማሪ ካለ ይመታል፡፡ ይህ በመሠረቱ ኢዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው። እንጭጭነትም ነው። ስለዚህ የኛ ትውልድ የዴሞክራሲ ትውልድ አይደለም፡፡ የአመፅ ትውልድ ነው፡፡ የፀረ ዴሞክራሲ ዘበኛ የነበረን ሥርዓት ግን በማስወገዱ እኮራበታለሁ። ከዚያ በኋላ አዲሱ ትውልድ ተረክቦ መሄድ ነበረበት፡፡ ሆኖም የእኛ ትውልድ አሁንም ሥልጣንን የሙጥኝ ብሎ አልለቅም በማለቱ አሁን ለሚታየው ቀውስ ምክንያት ሆኗል።
ሪፖርተር፡- ምን ማለት ነው ‹‹የሙጥኝ ብሏል›› ሲሉ? ለምሳሌ ኢሕአዴግ ውስጥ መተካካት እየተደረገ እንደሆነ ይሰማል፡፡ የመተካካቱን ሒደት አላመኑበትም?
ጄኔራል አበበ፡- መተካካት ሲባል የትውልድ መሆን አለበት፣ የግለሰቦች አይደለም። የአሁኑ ትውልድ ብቃት ያለው ትውልድ ነው። ገና ሲወለድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያውቅ፣ ከመንግሥት የተለዩ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን የሚያነብ፣ የተለያዩ ሐሳቦችን የሚያውቅ፣ ዓለም አቀፍ ትስስር ያለው፣ በምርምር ብዙ ነገር ማድረግ የሚችል ትውልድ ነው። ስለዚህ መተካካት ሲባል የትውልድ መጎራረስ ነው። ካለፈው ትውልድ በጎ በጎውን ተምሮ የራሱን ጥበብ ጨምሮበት እንደ ትውልድ አገሩን ሲረከብ ነው መተካካት የሚባለው።
ሪፖርተር፡- ‹‹የዴሞክራሲ ምኅዳሩ እየጠበበ ነው›› ብለዋል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግን ባልመጣበት የሰላማዊ ትግል መድረክ ማሸነፍ ስለማይቻል አዋጪውየትጥቅ ትግል ነው››የሚሉ ተቃዋሚዎች አሉ። የእርስዎ ግምገማ ምን ይመስላል?
ጄኔራል አበበ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ለውጥ እየተመዘገበ ነው። ይህ ለዴሞክራሲው ምን ማለት ነው የሚለው በደንብ መታየት አለበት። መንገድ ተሠራ ሲባል ሕዝቦች የሚገናኙበት፣ አንዱ የአንዱን ባህል የሚማርበት ዕድል ሰፋ ወይም ተፈጠረ ማለት ነው። ስለዚህ የትብብርና የአስተሳሰብ አድማሱ የሚሰፋበት ዕድል አለ ማለት ነው። የውኃ አገልግሎት ተሠራ ማለት ያቺ ሚስኪን ሴት አራት አምስት ሰዓታት ለውኃ የምታጠፋውን ጊዜ ትቆጥባለች ማለት ነው። ጤና ኬላ ተሠራ ማለት ጤንነቱ የተጠበቀ ልጅ መማር ይችላል ማለት ነው። የአንደኛ ትምህርት መስፋፋት ማለት እኮ ለዴሞክራታይዜሽን ሰፊ ምንጣፍ እየተነጠፈ ነው ማለት ነው። አባትም፣ እናትም ልጅም ለፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚሆን ጊዜ አገኙ ማለት ነው። በአጠቃላይ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው እየተቀየረ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ፍላጎቱ የሚጨምር ትውልድም እየተፈጠረ ነው። እዚህ ላይ ቅራኔ አለ፤ ሆኖም ይህንን ቅራኔ መፍታት የሚችል ትውልድ እየመጣ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ያጣው ቦታ ብቻ ነው። በትጥቅ ትግል ዴሞክራሲን ማስፈን የሚለው ነገር አስቂኝ ነው። ትጥቅ ትግል ለዚህች አገር አይረባም፣ በጣም አደገኛ ነገር ነው። የዴሞክራሲ ምኅዳሩ እየጠበበ መሄዱ ወደ ትጥቅ ትግል እንድትገባ ምክንያት ሊሆን አይችልም። በዚህ ጠባብ ሁኔታም ጭምር ጠንካራና እውነተኛ ፖለቲካዊ አመራር መስጠት የሚችል ካለ መታገል ይቻላል፡፡ ስለዚህም ነው በርካታ ዜጎች አገር ውስጥ እየታገሉ ያሉት። ምክንያቱም ሕዝቡ በቦታው ነው።
የኢትዮጵያ ዴሞክራታይዜሽን በኢሕአዴግ ፈቃድ ላይ የሚመሠረት ነገር አይደለም። በተወሰነ ሁኔታ ኢሕአዴግ ጥሩ በሚሆንበት ጊዜ ሒደቱን ሊያፋጥነው ይችላል ወይም በተቃራኒው ሊሆን ይችላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢሕአዴግን ፈቃድ መጠየቅ የለበትም። ሕዝቡ ይህንን ሥርዓት ያመጣው በራሱ ትግል ነው፡፡ የሚያስቀጥለውም ሕዝቡ ራሱ ነው። የ1997 ዓ.ም. ክስተት ሕዝብ ካመፀ ምን ማድረግ እንደሚችል ደንበኛ ማሳያ ነው። አሁን በኦሮማያና በትግራይ እምባሰነይቲ አካባቢ እየታየ ያለው የተደራጀ ሕዝባዊ የመብት ጥያቄ አለ። በሁሉም የሚታይ ባይሆንም አሁንም ኢሕአዴግ ውስጥ ሁሉንም ነገር በኃይል ለመፍታት የመፈለግና የመሞከር አዝማሚያ ይታያል። ይህንን የትጥቅ ትግል አስተሳሰብ አሽቀንጥረው መጣል አለባቸው። ምኅዳሩም ፍፁም ዝግ አይደለም፡፡ ጠባብ በመሆኑ ግን ብዙ መስዋዕትነትና ዋጋ ይጠይቃል።
ሪፖርተር፡- ሕዝባዊ አመፅ እየታየ ያለው በተካሄደው ምርጫ ገዢው ፓርቲ መቶ በመቶ ማሸነፉን በገለጸበት ማግሥት ነው፡፡ ይህን ያህል የሕዝብ ተቃውሞ መነሳቱ በምርጫ ሒደቱ ላይ ጥያቄ አያስነሳም?
ጄኔራል አበበ፡- የመንግሥትና የፓርቲ መዋቅሮች መደባለቅ አንዱ ትልቅ ችግር ነው። ኢሕአዴግ የመንግሥት ሚድያ፣ የመንግሥት ቢሮ፣ ገንዘብና አሉ የሚባሉ እርከኖችን ለፓርቲ ሥራ ስለሚያውል የፉክክር ሜዳው ዴሞክራሲን የሚያስችል (democracy enabling) እንዳይሆን አድርጎታል። ቻርለስ ቲሊ የሚባል ታላቅ የፖለቲካ ሳይንቲስት አንድ ፓርቲ ከሰባ አምስት በመቶ በላይ የፓርላማ መቀመጫዎችን ለብቻው ከያዘ ገና ከወዲሁ ዴሞክራሲያዊና ፍትሓዊ ያልሆነ፣ በሕዝብ ተቀባይነት የሌለው ምርጫ ነው ማለት ይቻላል ይላል። ምክንያቱም አንድ ሕዝብ ከፋብሪካ እንደሚወጣ ወጥ ምርት አይደለም። የተለያየ ፍላጎት፣ ምርጫና ዝንባሌ ስለሚኖረው። አሥር በመቶ እንኳ ተቃዋሚዎች ቢያሸንፉ መሬት ላይ ያለውን ሀቅ አያንፀባርቅም። የፌዴራሊዝም ባለሙያዎችና አገራዊ የውክልና ተቋማት ሕዝቡ ውስጥ ያሉ ልዩነቶችን ማንፀባረቅ አለባቸው ይላሉ። ስለዚህ ኢሕአዴግ አሽነፍኩ ያለበት ሒደትም የታወጀው ውጤትም አስቂኝ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ጭምር ነው። ውጤቱ ሲነገር ስቀን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ አደጋው ፈጦ እያየነው ነው። ኢሕአዴግ ማሸነፍ አይችልም ነበር እያልኩ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- እየታየ ያለው የአስተዳደር ቀውስ የሥርዓት ችግር (Systemic Problem) ነው ብለው በቅርቡ በጻፉት ጽሑፍ ላይ ተከራክረውነበር። በመፍትሔውላይም የሰጡት አስተያየት ነበር። ሥርዓታዊ ችግር ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ጄኔራል አበበ፡- መንግሥት ችግራችን የመልካም አስተዳደር ነው ብሎ ትልቁን ምሥል ወደ ጎን ትቶ ነገሩን ወደ ቴክኒካዊ ደረጃ አውርዶ ነው እያየ ያለው። እየተወሰደ ያለው ዕርምጃም ሥርዓቱን እንደ ሥርዓት የሚገመግምና የሚያስተካክል ሳይሆን፣ ታችኛው አመራርና ሲቪል ሰርቫንቱን ማዕከል ያደረገ ቁንፅል ነገር ነው። እኔ ደግሞ የምለው ‹‹ችግሩ ተራ የአስተዳደር ችግር ሳይሆን አጠቃላይ የዴሞክራሲ እጥረት የሚባል ነገር ነው፣ በአጭሩ ጉዳዩ የዴሞክራታይዜሽን ችግር ነው፤›› ነው። ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትና አሠራሮች ከመሥራት ወይም ካለመሥራታቸው የተያያዘ ነው። ቀላል ነገር አይደለም። መዋቅራዊ ችግርን አድበስብሶ ማለፍ ውጤቱ እስከ አገር ማፍረስ ሊዘልቅ ይችላል፡፡ ነገርየውን መመርመርና መፈተሽ ያለብንም ከዚህ አቅጣጫ ነው። ከሁሉም በላይ ግን የሕዝቡን የተደራጀና የተናጠል ትግል ለማፈን የሚደረጉ ነገሮች ስለችግራችን ስፋትና ዓይነት ብዙ ነገር ይነግሩናል።
ሲቪል ማኅበረሰቡም ቢሆኑ የፓርቲ ተቀጥያ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ያለው፡፡ ሥራ ለማግኘት አባልነትና ድጋፍ መለኪያ ሲሆን ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ጥሰት መሆኑን መገንዘብ አለብን። ለምሳሌ ኦሮሚያ ውስጥ የተነሳውን ሕዝባዊ አመፅ ብንመለከት ለዴሞክራሲ ትልቅ ግብዓት ይሆን ነበር፡፡ መንግሥት ብስለቱና ብልኃቱ ስለሌለው በተወሰነ መልኩም ቢሆን ፅንፈኞችና አክራሪዎች ሕዝቡ በማይፈልገው መንገድ ለመጠቀም ችለዋል፡፡
እነዚህ ኋላቀር ፅንፈኞች ደግሞ ይህንን ተገቢ ትግል በሕዝቦች መካከል ጥርጣሬ እንዲሰፍንና ግጭት እንዲቀሰቅሱበት ለመጠቀም ሞከሩ፡፡ በተወሰነ ደረጃም ተሳካላቸው። ጥያቄው ሕዝቡ ወዳልፈለገው አቅጣጫ ለመውሰድ የሞከሩ ፅንፈኞች የአቅማቸውን ያህል ቢጥሩም የሕዝቡ ጨዋነት ግን የሚገርም ነበር፡፡ ይህ ጨዋ ሕዝብ ላይ የደረሰው ሞት፣ የአካል ጉዳትና ውድመት በጣም አሳዛኝ ነው። ከዚህ ሒደት የምንማረው በገዢው ፓርቲና በሕዝቦች መካከል ትልቅ ክፍተት እንዳለ ነው። ሕዝቦች በገዢው ፓርቲ መሪነት አንድ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ኢሕአዴግ ግን ቆሟል ወይም ወደኋላ እየነጎደ ነው። ከሕዝቦች ፍላጎትና ዕድገት ጋር አብሮ መሄድ አልቻለም።
ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ‹‹ሕዝቡን አስለቅሰነዋል፣ በድለነዋል››ብለዋል። ይቅርታምጠይቀዋል።
ጄኔራል አበበ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንደዚያ ማለታቻው የሚመሠገን ተግባር ነው፡፡ አንድ ዕርምጃ ወደፊት መሄድ ነው። በኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትሩ በኩል የሚገለጸው ነገርም አንዳንዴ ተስፋ የሚሰጥ ነው። ይቅርታ ማለት ሕዝብን ማክበር ነው፣ ትልቅነት ነው። ይቅርታ ማለት መጀመሩ በራሱ እንደ ትልቅ ነገር አድርጌ ነው የምቆጥረው። ለዚህም ማመስገን እፈልጋለሁ። ይቅርታ ብቻውን ግን በቂ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ችግሩ መላውን ኢትዮጵያ የሚያስለቅስ ከሆነ ነገሩ ሥርዓታዊ ነው ማለት ነው። ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበትም ይህ ችግር ከየት ይመነጫል የሚለው ነው። የፍትሕ መጓደል፣ ሙስና፣ አስተዳደራዊ በደል በተለያየ መጠን ይኖራሉ፡፡ ሆኖም የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ሲጠብ ችግሮቹ ይጎለብታሉ፡፡ በተቃራኒው የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ሲሰፋ ችግሮቹ ይቀጭጫሉ፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ ይሳተፋል፡፡ በሰላማዊ ሠልፍ፣ ሐሳቡን በነፃነት በመግለፅ፣ በነፃ በመደራጀትና በመሳሰሉት ይሳተፋል። ኢዴሞክራሲያዊ ኃይሎችና ክራይ ሰብሳቢዎችን ይታገላቸዋል ማለት ነው፡፡ ለግላዊና ለቡድናዊ መብቱ ዘብ ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ ችግሩን ሲገመግሙ ከላይ ከቁንጮው ነበር መገምገም የነበረባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የቀረበው ጥናት ጥሩ ነበር፡፡ ቀጣይ ዕርምጃዎቹ ግን መሠረታዊ ስህተት ነበረባቸው፡፡ ከላይ መጀመር ሲገባው የሆነው በተገላቢጦሽ ነበር።
ሪፖርተር፡- ‹‹በተገላቢጦሽ›› ሲሉ ምን ለማለት ነው?
ጄኔራል አበበ፡- ጥናቱ መገምገም የነበረበት መዋቅራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ነበር። በፓርቲና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት፣ የዳኞች አሿሿም፣ የከፍተኛ ባለሥልጣናት የምልመላና የግምገማ ሥርዓት፣ በፓርላማውና በሥራ አስፈጻሚው መካከል ስላለው ግንኙነት፣ የሚዲያው ሁኔታ፣ የፍርድ ቤቶች ነፃነት ነበር መገምገም የነበረበት፡፡ በፓርቲውና በሕገ መንግሥቱ መካከል የሐሳብ ቅርበት ወይም ልዩነት አለ ወይ ብሎ መገምገም ነበረበት። ነፃ የሆኑ የሕዝብ አደረጃጀት አለ ወይ? የግል ፕሬሱና ሲቪል ማኅበረሰቡ በነፃ ይንቀሳቀሳሉ ወይ? ፓርቲዎቹስ መተንፈሻ አግኝተዋል ወይ ብሎ መታየት አለበት። ሲጠቃለል ሕዝቡ ትርጉም ያለውና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያስችል ሁኔታ አለ ወይ ብሎ ነው መገምገም ያለበት። በአስገዳጅ ስብሰባዎች እጅ እንዲያወጣ ማድረግ አይደለም ተሳትፎ ማለት። አንዳንድ በጎበኘሁዋቸው አካባቢዎች ‘አንድ ለአምስት’ የሚባል አደረጃጀት አደገኛ የስለላ መዋቅር እየሆነ ነው። ማኅበራዊ እሴቶቻችንን የሚበጣጥስና ማኅበራዊ ኑሮን ሊያናጋ በሚችል መንገድ ሥራ ላይ እየዋለ ሳይ በጣም ደንግጬያለሁ። ባልና ሚስት፣ ልጆችና ወላጆች በአጠቃላይ ቤተሰብ ቤተሰቡን የሚሰልልበትና የሚያስፈራራበት አሠራር እየሆነ ያለበት አጋጣሚ ስላለ ቆም ብሎ ማሰብ ይጠይቃል። ቤተሰብን ይበትናል። አደረጃጀቱም በኃይል ስለሆነ ግለሰባዊ ቅንነትንም ይገድላል። ስለዚህ ኢዴሞክራሲያዊ እየሆነ የመከባበር፣ የመተማመንና የአብሮነት እሴቶችን ይገድላል። በዘመናት የተገነባ እሴት በዓመታት ዋጋ ቢስ ሆኖ ብዙ ዋጋ እንዳያስከፍለን እሠጋለሁ።
ሪፖርተር፡- በቅርቡ በትግራይ ክልል የእምባሰነይቲ ሕዝብ ‹‹ወረዳችን ይመለስልን›› የሚል ጥያቄ አንስቷል። ይህ ሕዝብ የሕወሓት ኮር ቤዝ የሚባልነበር። በድርጅቱየተሰጠው መልስና ጥያቄው እንዴት ያዩታል?
ጄኔራል አበበ፡- በመጀመርያ የእምባሰነይቲ ሕዝብ እንደዛ ጨዋነት በተሞላው፣ የሞራል ልዕልናውን ባረጋገጠ መንገድ ጥያቄውን በተደራጀ መንገድ ማቅረቡ ሊያስመሰግነው ይገባል፡፡ እኔም በግሌ ያለኝን ልባዊ አክብሮት መግለጽ እወዳለሁ። በዚህ ሒደት ሁለት ነገሮች አሉ። የሕዝቡ ተገቢ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ መንግሥትም ያገባኛል ማለቱ የግድ ነው፡፡ የበጀትና ተያያዥ ነገሮች ስላሉ። መንግሥት ግን ሲያገባው እንዴት ነው መልስ የሚሰጠው የሚለው መታየት አለበት። መጀመሪያ ጥያቄ ለምንድነው ወረዳ የሚፈልገው የሚለው ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር አስተሳስሮ መመለስ ነበረበት፡፡ ይህ ለሃያ ዓመታት የቆየች ችግር በጥናት በተረጋገጠ መንገድ አልተመለሰም። የሕዝቡን ጥያቄ አክብሮ ከማዳመጥ ይልቅ የት ትደርሳላችሁ የሚል የትዕቢት መልስ መንግሥት መስጠቱን ሕዝቡ በሰላማዊ ሠልፉ ላይ ገልጿል፡፡ ይህ አሳፋሪና አሽማቃቂ መልስ ነው። ይህ ሕዝብን መናቅ ነው፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ እየጠፋ ነው ማለት ነው፡፡ ከሕዝብ ጋር ሆነህ መፍትሔ መሻት የሚባል ነገር የለም ማለት ነው። ሰማንያ አንድ ወረዳ ቢፈጠር ለልማት እንቅፋት ይሆናል የሚል ሥጋት እንኳን ቢኖራቸው፣ ሥጋታቸውን ከሕዝቡ ጋር ሆነው ተመካክረው ወረዳ መሆን የሚሰጠውን ጥቅም በሆነ አሠራር ሕዝቡ እንዲያገኝ ለማድረግ ፍላጎት አለማሳየታቸው ያሳዝናል። ነገሩን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ጥያቄው የእምባሰነይቲ ብቻ አለመሆኑን እያወቁ ማስፈራራትን እንደ መፍትሔ መውሰዳቸው ነው።
ችግሩ የኪራይ ሰብሳቢ፣ የጥገኛ አመራር፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ሴራ አድርገው ማየታቸው ምን ማለት እንደሆነ የገባቸው አይመስለኝም፡፡ ሕዝቡን ሞኝ ነህ፣ ተታለህ ነው፣ ስለራስህ ምንም አታውቅም እያሉት ነው። ይህ ደግሞ ከማሳዘን አልፎ ከባድ አላዋቂነት ጭምር መሆኑን ነው የሚያሳየው። በኦሮሚያም የተባለው ተመሳሳይ ነው፡፡ በሁሉም ክስተቶች የእገሌ የእገሌ እየተባለ ሕዝብን ማሸማቀቅ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት መሆኑ መታወቅ አለበት። ሲጀመር መንግሥት የት ነበርና ነው?
ሪፖርተር፡- ከኦሮሚያ ቀጥሎ በቅርቡ የታጠቀ ኃይል በሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ላይ የበላይነት ከያዘ፣ የፖለቲካ ፍላጎት ሊያሳድር ይችላል የሚል አስተያየትም ሰጥተው ነበር፡፡ ዕውን በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሥጋት ይኖራል?
ጄኔራል አበበ፡- የደኅንነትና የዴሞክራሲ እጥረት ዋናው የድህንነታችን ጥያቄ ነው። በአፍሪካ እንደምናየው የታጠቀው ኃይል ከትጥቅ በላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ተፅዕኖ አለው። በሲቪል ቁጥጥር ሥር ካልዋለ ራሱን ንጉሥ ወይም አንጋሽ የመሆን ፍላጎት ሊያዳብር ይችላል። ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ሕጉ በሚያስቀምጠው መንገድ መሥራት ካልቻሉ አጠቃላይ መዛባት ይፈጠራል። ሕገ መንግሥቱ በተለያዩ ተቋማት መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት በሥርዓቱ ደንግጓል፡፡ ሕጉ በተገቢ መንገድ በማይተገበርበት ጊዜ ግን መዛባት ይፈጠርና ጉልበት የበላይነት ያገኛል። ሥልጣን አስፈጻሚው ዘንድ ሲጠቃለል የመጀመሪያው የአደጋ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ከአስፈጻሚው ጋር ደግሞ ሲቪልና የደኅንነት አካላት አሉ። እዚህ ጋ መዛባት ሲፈጠር ጠቅላላ ኃይሉ ወደ ታጠቀው ይጠቃለላል። ካልተዛባ ቦታውን ይይዛል፣ አገሩንም ይጠብቃል፣ የውጭ ጠላትን ይመክታል ይከላከላል። ካልሆነ ግን ፖለቲካዊ ፍላጎት አዳብሮ ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል። ሕገ መንግሥቱ መሠረት ተደርጎ ካልተኬደ ሲቪሉ በታጠቀው ኃይል ሥር ይወድቃል። አሁን አንዳንድ ምልክቶች እየታዩ ነው። ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ተያይዞ የተሰማው ነገር የዚህ ምልክት ነው እንዴ? እንድትል ያደርጋል።
ሪፖርተር፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየመን የሳዑዲ ዓረቢያ እንቅስቃሴ አለ፡፡ ከደቡብ ሱዳን የመጡ ታጣቂ ቡድኖች በጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ላይ ብዙጉዳት አድርሰዋል፡፡ቀጣይነት ያለው ከኤርትራ የሚመጣ አደጋ አለ። እርስዎ እንደ የሰላምና የደኅንነት ባለሙያና የቀድሞ ጄኔራል እንደመሆንዎመጠን በዚህ የደኅንነት ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
ጄኔራል አበበ፡- ባለሙያ ለመባል እንኳን ያስቸግረኛል። ጋምቤላ ላይ የተፈጠረው ትልቅ ጉዳይ ነው። ብዙ ሰው ነው የሞተውና የተጎዳው። ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፅናቱን እንዲሰጣቸው እመኛለሁ። ለብቻው ስታየው የሚያጋጥም ነገር ነው ለማለት የሚቻል ይሆናል። ነገር ግን ብዙ ጥያቄዎች ያሉበት ነው። ሙርሌዎች እንዴት ብለው ነው ልባቸው ሞልቶ ለቀናት ተዘጋጅተውና ሠልጥነው ያጠቁት? እንዴት ብለው ነው የደፈሩት? እዚያ አካባቢ ያለው የደኅንነትና የመከላከያ ኃይሎች ምን ይሠሩ ነበር? በአካባቢው ሠራዊት ነበር? አልነበረም? ለምንድነው በአጭር ጊዜ ምላሽ ያልተሰጠው? ሕፃናቱን ማስመለስ ለምንድነው የዘገየው? ሲደጋገምና ተመሳሳይ ክስተቶች በርከት ብለው ሲታዩ ጥያቄ መነሳቱ የግድ ነው። ይኼ ነገር የሥርዓቱ ችግር ሊሆን ይችላል ተብሎ ከብሔራዊ የደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ ከፖሊሲው ማኔጅመንት፣ ከሥራ አስፈጻሚውና ከተወካዮች ምክር ቤት ሚና ጋር አያይዞ ማየት ያስፈልጋል። የሥርዓቱ በሽታ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ፓርላማው ሐዘን ከማወጅ የዘለለ ለምን ተከሰተ ብሎ አስፈጻሚውን መጠየቅና ማጣራት አለበት፡፡ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥንም ቢሆን ይህ ነገር ለምን ተከሰተ ተብሎ ሊጠየቅና ማብራርያ ሊሰጥ ይገባዋል። መከላከያ ሚኒስትሩም እንዲሁ። ይህ ክስተት ሥርዓቱን እያስተካከልን እንሄዳለን የሚል በጎ አስተሳሰብ ካለ አጠቃላይ ሥርዓቱን ለመፈተሽ ይጠቅመናል፡፡ ክስተቱ የውድ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈ አሳዛኝ ድርጊት መሆኑ ሳይረሳ።
ሳዑዲዎች የኤርትራ ባህር ዳርቻዎች ላይ የጦር መርከቦቻቸው ሲያሰፍሩ ኢትዮጵያን አንነካም፣ ዓላማችን የመን ላይ ነው እያሉ ይምላሉ ይገዘታሉ፡፡ እኛ እንደ ሞኞች ብለውናል ብለን ነው መሄድ ያለብን? የፈለጉትን ነገር ለማድረግ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው? ሳዑዲ ዓረቢያ አሥራ አምስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ በሱዳን ኢንቨስት እያደረገች ነው፡፡ ለሱዳን ወታደራዊ ድጋፍ እየሰጠች ነው፡፡ ሱዳን ሠራዊትዋን ወደ የመን ልካለች፡፡ በሳዑዲና በኢራን መካከል ከነበረው ፍጥጫ ተነስተው ሱዳንና ሶማሊያ ከኢራን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል። ይኼ የሱዳንና የኢራን እንጂ እኛ ጋ ሊከሰት አይችልም የሚባል ነገር ልክ አይደለም። አጠቃላይ ሁኔታው ምን ይመስላል የሚለው ነገር መጤን አለበት። የኤርትራም ጉዳይ ከዚህ ጋር ተያይዞ ነው መታየት ያለበት።
ሪፖርተር፡- በቀጣናው እየታየ ያለውን የደኅንነት ሥጋት ለመቆጣጠር ከውስጥ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ጄኔራል አበበ፡- በዚህ ጊዜ ደግሞ ለዘመናት የኢሕአዴግ ባህል የነበረው የጋራ አመራር እየጠፋ ነው፡፡ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ባልተቋመበት፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ ጽሕፈት ቤት ባልነበረት ሁኔታ አደጋ ተከስቷል። በዚህ ላይ አንድ የጻፍኩት ጽሑፍ አለ። በጥናቴ ያገኘሁት ነገር ቢኖር ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት በአዋጅ ቢቋቋምም፣ ሴክሬታሪያት የሌለውና አልፎ አልፎ እንደሚሰበሰብና የተጠናከረ አደረጃጀት እንደሌለው ነው። የዚችን ትልቅ አገር ደኅንነት በዚህ መልኩ መያዝ የለበትም፡፡ ጥንቃቄና ጥልቅ ትንተና የግድ ነው። ከየዘርፉ ምሁራን መሰብሰብ አለባቸው፡፡ ሥጋቶችና ፀጋዎች በደንብ መለየት አለባቸው፡፡ ትንበያዎችና ቅድመ ዝግጅቶች መደረግ አለባቸው። ነገሮች ከተፈጠሩ በኋላ እሳት ለማጥፋት አይደለም መሮጥ ያለብን፡፡ ሊፈጠር እንደሚችል መገመት የሚያስችል አቅም ልንገነባ ይገባናል፡፡ ታላቅ አገር ይዘን ንህዝላል መሆን አንችልም። የሁሉም የትምህርት ተቋማት፣ ኤምባሲዎችና ቆንፅላ ጽሕፈት ቤቶች፣ የደኅንነትና የወታደራዊ መረጃ፣ የቲንክ ታንኮችና ዓለም ላይ ሊገኙ የሚችሉ መረጃዎችን መሠረት እያደረገ ሴናርዮዎች (ቢሆኖች) ማቅረብ የሚችል በትልቅ አቅም የሚንቀሳቀስ የደኅንነት ሴክሬታሪያት ያስፈልገናል። ለምሳሌ ከተቋማዊ አሠራር አቅጣጫ ብናየው በተከታታይ የኤርትራ መንግሥት ሉዓላዊነታችንን እየደፈረ ዜጎቻችንን ይጠልፋል፣ አልፎ አልፎ ይመለሳሉ፡፡ ፓርላማው ግን አንድም ቀን ቢሆን አስፈጻሚውን ለምን እንዲህ ሆነ ብሎ ሲጠይቅ ዓይተን አናውቅም። ሙርሌዎች እንደዚህ ሲያበሳብሱን ፓርላማው ለምን ማለት ነበረበት፡፡ የሚመለከተው አካል መጠየቅና ኃላፊነት መውሰድ ነበረበት።
ሪፖርተር፡- ከኢሕአዴግ ነባር አመራሮች ወጣ ያለ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ያጣችው ‹‹በኢሕአዴግ አላዋቂነት ነው›› ብለዋል፡፡ በጥናታዊጽሑፍዎ ድምዳሜምሰፍሮ ይገኛል። እውነት ሕጋዊ መሠረት አለን ማለት ነው?
ጄኔራል አበበ፡- ድሮም ቢሆን የኤርትራን ነፃነት ተቀብለው የአሰብ ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች ነበሩ። እንደነ አቶ ተወልደ ወልደ ማርያም፣ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳኤ፣ አቶ ስየ አብርሃ፣ አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ እኔም ጥያቄዎች የምናነሳበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዝርዝር ባንወያይበትም። አሜሪካ ሄጄ ሁለተኛ ዲግሪዬን ስሠራ ግን በዚህ ላይ ጥናት አካሂጄ የባህር በር መብታችንን በሕጋዊ መንገድ ማስመለስ እንደምችል የሚያረጋግጥ ድምዳሜ ላይ ደረስኩ። ባለማወቅና በመታበይ (Ignornace and arrogance) ያጣነው መብት ነው፡፡ አሁንም ግን ሕጋዊ መሠረት አለን፡፡ ዝርዝር ነገር የሚፈልግ ካለ የመመረቂያ ጽሑፌ ላይ አስፍሬዋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በአሰብ ጉዳይ ላይ ካደረጉት ጥናት ውጪ በተግባር የመሥራት ዕቅድ አለዎት?
ጄኔራል አበበ፡- አዎ፡፡ የአገር ጉዳይ ስለሆነ ነው። በእኔ አረዳድ የባህር በር ሳናውቅ ያጣነው አገራዊ ፀጋችን ነው። በእርግጥ የባህር በር ጉዳይ ከአጠቃላይ ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ሥርዓቱ አንፃር ካልታየ የወራሪነት ባህሪ ያለው አደገኛ ነገር ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህም ተጠንቅቄ የማነሳው ጉዳይ ነው። የባህር በር ጉዳይ በጣም አስፈላጊ ነው ስል የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጌ አላየውም። ከኢኮኖሚም ከፀጥታም አኳያ በጣም ያስፈልገናል፡፡ ግን ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ነው መሆን ያለበት። አሁን ያለውን ሥርዓትና መሠረታዊ የፖለቲካ እሴቶቻችን በሚንድ መልኩ መሆን የለበትም። አሁን ያለን ሕገ መንግሥት ለሌሎች ሕዝቦችና አገሮች አርዓያ መሆን የሚችል የዳበረ ሕገ መንግሥት ነው። ስለዚህም የአሰብ ጉዳይ ተነስቶ ሕገ መንግሥቱን ለመሸርሽርና ለመናድ በሚደረግ እንቅስቃሴ አልሳተፍም። ይህ ሕጋዊ መብታችን ግን መረጋገጥ አለበት ብዬ ስለማምን በቻልኩት መጠን እንቅስቃሴ አድርጋለሁ።
ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ ከክፍፍሉ ከ1993 ዓ.ም. በፊትና በኋላ እንደ ድርጅት ውስጣዊ ጥንካሬው እንዴት ያዩታል?
ጄኔራል አበበ፡- ኢሕአዴግ በ1993 ዓ.ም. ቀውስ ውስጥ ሲገባ የድርጅቱ አባል አልነበርኩም፡፡ የአየር ኃይል አዛዥ ነበርኩ። ስለዚህ ድርጅት ውስጥ የነበረውን ነገር በዝርዝር አላውቅም፡፡ ሆኖም ከሁለቱም አንጃዎች በኩል የትጥቅ ጊዜ ጓደኞቼ ስለነበሩ በሁለቱም ጎራ የነበረውን ሁኔታ እሰማ ነበር። ከድርጅቱ ጋር በነበረን ሥነ ልቦናዊ ትስስርም ድርጅቱ እንዲፈርስ አንፈልግም ነበር። ቁውሱን ለመፍታት የተደረገው ድርጊት ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ጠባሳ ያሳደረ ነበር። ሒደቱ እልባት ያገኘው ኢዴሞክራሲያዊና ኢሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ነበር። የመንግሥት ሚዲያ የአሸናፊው አንጃ ሚዲያ ሆኖ ተሸናፊው አንጃ ሐሳቡን የሚገልጽበት ዕድል ተነፍጎ፣ ጄኔራሎችም ጭምር በጉዳዩ ፖለቲካዊ መግለጫ የሰጡበት ሕገ መንግሥታዊነት፣ ፌዴራሊዝምንና የድርጅትን ሕገ ደንብ ገደል የከተተ ሒደት ነበር። ለስዬ ተብሎ ሕግ እስከማውጣት ድረስ ተኪዷል፡፡ ፍርድ ቤት ሲለቀው ፖሊስ በጉልበት ይዞታል። በአጠቃላይ የቀውስ አፈታት ሒደቱ ኋላቀር ብቻ ሳይሆን የተወው ትምህርትም አደገኛ ነው። በውስጥ የፓርቲዎችን መብትም የናደ ነበር። በተለይ ኦሕዴድና ደኢሕዴን ላይ የተሠራው ሥራ ህልውናቸውንና ነፃነታቸውን በሚንድ መልኩ ነበር የተካሄደው። በዚያ መልኩ መለያየታችን ያሳዝነኛል።
ሪፖርተር፡- በ1993 ዓ.ም. የተከሰተውን ቀውስ በመፍታት ረገድ የታየው ፀረ ዴሞክራሲ አሠራር ከዚያ በፊት አልነበረም ይላሉ?
ጄኔራል አበበ፡- መለያየቱ ራሱ የነበረውን አቅም የበተነ ነበር፡፡ ትልቅ ብቃትና ዕውቀት የነበራቸው ሰዎች በአገር ግንባታ እንዳይሳተፉ ያደረገ ነገር በመሆኑ ያሳዝነኛል። በተጨማሪም አሸናፊው አንጃ የደኅንነት መዋቅሩን የሰው መብት በሚጥስና ፍራቻን ለማንገሥ ባለመ ሁኔታ ነበር ሲያንቀሳቅስ የነበረው። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌዎች ከዚያ በፊት አልነበሩም ማለቴ አይደለም። ምናልባት እኛ ላይ ስለተፈጸመ ሊሆን ይችላል ያስተዋልነው ወይም መጠኑ ከፍ ብሎ ሊሆን ይችላል። በሰዓቱ የነበረን አስተሳሰብ ‹ከኢሕአዴግ መስመር ውጪ ሁሉም የጥፋት መስመር ነው› ብሎ የሚያምን ስለነበር ተቃዋሚዎችን እንደ ፀጋ የማያይ፣ እግራቸውን እንዳይተክሉ የሚያደርግ አስተሳሰብ ነበር፡፡ ጎልቶ የታየን ግን እኛ ላይ ሲደርስ ነው። ስለዚህ 1993 ዓ.ም. ብቻውን መለያ አይሆንም። እንደኔ አመለካከት ኢሕአዴግ የተሻለ ዴሞክራቲክ ድርጅት ነበረ ብልም ሙሉ በሙሉ ዴሞክራቲክ ነበር ለማለት አልችልም። ከቀውሱ በፊት ፓርላማው ማኅተም መቺ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቶች ነፃነት አልነበራቸውም፡፡ ‹ቼክ ኤንድ ባላንስ› የነበረበት የሥልጣን ክፍፍል አልነበረም፡፡ ከዘጠና ሦስት በኋላ ግን ባሰበት።
ሪፖርተር፡- ለወጣቱ ትውልድ ምን ይመክራሉ?
ጄኔራል አበበ፡- ወጣቱ ትውልድ ያለፈው ትውልድ የሠራውን ሥራ ዕውቅና እየሰጠ ሲያበላሽ ደግሞ አታበላሽ ማለት መቻል አለበት፡፡ ያለውን ብልሽት ለማስተካካል መሥራት አለበት፡፡ ማማረር ብቻ መፍትሔ አይሆንም። በምሬት መጀመር ባህርያዊ ነው። ወጣቱ ትውልድ በሚያምንበት አደረጃጀት እየገባ መታገል አለበት። በግልና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሸሸጉ ማፊያዎችን መታገል አለበት። አገሪቷ በመስቀለኛ መንገድ ነው ያለችው፡፡ የወጣቱ ፖለቲካዊ ተሳትፎ የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው። በፌስቡክም፣ በትዊተርም፣ በየጋዜጣና በየመጽሔቱ በትጋት የሚሳተፉ ወጣቶችን በርቱ ማለት እወዳለሁ።
No comments:
Post a Comment