ሚያዚያ 03 ቀን 2008 ዓ.ም.ዜና (April 11, 2016 NEWS)
#የተወሰኑ የደቡብ ሱዳን አማጽያን ወታደሮች በስምምነቱ መሰረት ጁባ ገቡ
#በቻድ በኮሞሮና በዳርፉር ምርጫዎች ተካሄዱ
#በሱማሊያ የፈነዳው ቦምብ ጉዳት አድረሰ
Ø የደቡን ሱዳን አማጽያን መሪ ሪክ ማቻር ሚያዚያ 10 ቀን 2008 ዓ.ም ዋናዋ ከተማ ጁባ ይገባሉ ተብሎ ቀደም ብሎ የተነገረ ሲሆን ቀደም ብሎ በተደረገው ስምምነት መሰረት የምክትል ፕሬዚዳንቱና የሌሎች ባለስልጣናትን ደህንነት ለመጠበቅ 1370 የሚሆኑ የደቡብ ሱዳን አማጽያን ወታደሮችና የፖሊስ አባላት ጁባ ከተማ የገቡ መሆናቸው ተዘግቧል። ወታደሮቹ ወደ ከተማ የገቡት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አውሮፕላን ሲሆን የተመደበላቸውን ቦታ ይዘዋል ተብሏል። በአማጽያኑና በደቡብ ሱዳን መንግስት መካከል ባለፈው ዓመት የተደረገው ስምምነት ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጣ አነስተኛ የወታደርና የፖሊስ ኃይል ብቻ በከተማዋ እንዲኖር የሚወስን ሲሆን ይህኛው የመጀመሪያው ዙር መሆኑ ታውቋል። የደቡብ ሱዳን አማጽያን ቡድን ቃል አቀባይ በሰጠው መግለጫ የደቡብ ሱዳን መንግስት ጁባ ውስጥ የሚገኙትን ወታደሮችና ፖሊሶች በስምምነት መሰረት ያልቀነሰ መሆኑን ገልጾ እንዲያውም የወታደሩ ቁጥር ከነበረብት ጨምሯ የሚል ክስ አሰምቷል።
Ø እሁድ ሚያዚያ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በቻድ በኮሞሮ ደሴቶችና እና በሱዳን ዳርፉር ግዛት ምርጫዎች ተካሄደዋል። በቻድ በተካሄደው ምርጫ ከሃያ ስድስት ዓመት በፊት በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ላይ የወጡት ኢድሪስ ዴቢ እና ሌሎች 12 ግለሰቦችም ተወዳዳሪ ሆነው ቀርበዋል። በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የማጭበረበር ተግባሮች በየቦታው ተከስተዋል፤ ወታድሮች መራጩ ሕዝብ ድምጹን ለፕሬዚዳንቱ እንዲሰጥ አስገድደድዋል፣ በአንዳንድ ቦታም ድምጾች በገንዘብ ተገዝተዋል የሚሉ ክሶች መንግስቱን ከሚቃውሙ ተወዳዳሪዎች ቀርበዋል። የመራጩ ብዛት ከፍተኛ መሆኑ የታየ ሲሆን ታዛቢዎች ፕሬዚዳንቱ ያሸናፋሉ የሚል ግምት ሰጥተዋል። ከአስራ ሶስት አመታት በፊት በሀገሪቱ ውስጥ የነዳጅ ምርት ተገኘ ቢባልም ከአገሪቱ ሕዝብ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነው ከድህነት እርከን በታች እንደሚኖር ተዘግቧል። ከ10 የቻድ ዜጎች መካከል 7 ቱ መጻፍና ማንበብ የማይችሉ ማሃይማን መሆናቸውም የተመድ ምንጮች ይገልጻሉ። በመንግስት ላይ ያለው ተቃውሞ ከፍተኛ ሲሆን የጽጥታ ኃይሎችም ከፍተኛ አፈና ግድያ በሰፊው እንደሚያካሄዱ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ አቅርብዋል።
በኮሞሮ የአሁኑኑ ፕሬዚዳንት ለመተካት የሁለተኛ ምርጫ ሚያዚያ 2 ቀን ተካሄዷል። ምርጫው የተካሄደው በመጀመሪያ ዙር ምርጫ ከፍተኛ ድምጽ ባመጡት በሶስት ተወዳዳሪዎች መካከል ሲሆን ውጤቱ ከረቡዕ በፊት አይታወቅም ተብሏል። በጥር ወር በተካሄደው በመጀመሪያ ዙር ምርጫ 19 ተወዳዳሪዎች ምርጫው ማጭበርበርና ማታለል የበዛበት ነው በማለት መክሰሳችው ይታወሳል።
ለረጅም ጊዜ የእርስ በርስ ጦርነት ሲካሄድበት በቆየው በሱዳን የዳርፉር ግዛትም ለሶስት ቀናት የሚቆየው የውሳኔ ሕዝብ ምርጫ እሁድ ሚያዚያ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ተጀመሯል። የበሽር መንግስት ዳርፉር በአምስት የግዛት አስተዳደሮች ይከፋፈል ወይስ በአንድ አስተዳደር ስር ይቆይ የሚለውን ሀሳብ ሕዝብ እንዲወስነበት ምርጫውን ያዘጋጀ ሲሆን አንድ የአስተዳድር ግዛት ነው የሚያስፈልጋት የሚሉት ተቃዋሚዎች ሀሳቡን ተቃመው መራጩ እንዳይሳተፍ ጥሪ አድርገዋል፡፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሁን ዳርፉር ውስጥ በሚገኘው የጸጥታ ሁኔታ ትክክለኛ ምርጫ ሊካሄድ አይቻልም ብሏል። እስካሁን ድምጹን ለመስጠት የወጣው ዜጋ በጣም አነስተኛ መሆኑ ሲነገር ብዙዎችም ወደ ምርጫ የወጡት በወታደሮች እየተጃቡ መሆናቸው ተገልጿል።
Ø ሰኞ ሚያዚያ 3 ቀን 2008 በስማሊያ ዋና ከተማ በሞጋዲሹ በአንድ የምግብ ቤት አቅራቢያ የፈነዳው ቦምብ ቢያንስ አምስት ሰዎች የተገደሉ መሆናችው የዓይን እማኞች ገለጹ። ሬስቶራንቱ የሚገኘው ሀመረወይን በሚባለው አካባቢ ከከተማው አስተዳድር አቅራቢያ በመሆኑ የመንግስት ሰራተኞችን ለመጉዳት ሆን ተብሎ የተወሰደ እርምጃ ነው በማለት ታዛቢዎች ግምታቸውን ይሰጣሉ። ለፍንዳታው እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ ግለስብ ወይም ቡድን ባይኖርም አለሸባብ እንደሆነ ይገመታል፡፡ የዛሬው የቦምብ ፍንዳታ የደረሰው ቀደም ብሎ ኬኒያ ውስጥ ተይዞ ወደ ሱማሊያ እንዲመጣ የተደረገና ጋዜጠኞች ገድሏል ተብሎ የተፈረደበት አንድ የበጥይት ተደብድቦ ተገድሏል የሚል ይፋ መግለጫ የሱማሌ መንግስት በሰጠ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነው።
No comments:
Post a Comment