Friday, April 15, 2016

የፍኖተ ዴሞክራሲ ራድዮ አጫጭር ዜናዎች – ሚያዝያ 6, 2008

ሚያዚያ 06 ቀን 2008 ዓ.ም.ዜና (April 14, 2016 NEWS)
#በኢትዮጵያ የገባው ድርቅና ረሃብ እየከፋ መጣ ተባለ
#የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ቀነሰ ተባለ
#በወያኔ በግፍ ታስሮ የነበረው ጋዜጠኛ ተፈታ
#ባህር ዳር በወያኔ የጸጥታ ኃይሎች ተወራለች
#በጃፓን የመሬት መንቀጥቀጥ ደረሰ
#ከሁለት ዓመት በፊት በናይጄሪያ በቦኮሃራም ከተጠለፉ ልጃገረዶች
#መካከል አንዳንዶቹ በህይወት መኖራቸው በቪዲዮ ታየ
#በብሩንዲ በጸጥታ ኃይሎች የሚወሰዱ ሰዎች መዳረሻቸው እየጠፋ ነው ተባለ
#የአውሮፓ ህብረት መልእክተኞች ቡድን ሊቢያ ገባ


hailemariam
Ø የወያኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያ ደሣለኝ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሰባት ከመቶ ያድጋል ሲል አማካሪው አርከበ እቁባይ ደግም 11 ከመቶ ያድጋል ብሏል። የወያኔ የጡት አባት የሆነው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት IMF ደግሞ የወያኔን የኢኮኖሚ እድገት ወደ 4.5 ከመቶ ያወርደዋል። የገንዝብ ድርጅቱ የወያኔ የኢኦኖሚ እድገት ያስቆለቆለው በኢትዮጵያ ባለው ድርቅና ረሃብ በዓለም አቀፉ የገበያ ዋጋ መቀነስ ነው ይበሉ እንጅ የወያኔ ኢኮኖሚ ወትሮም ቢሆን የፕሮፓጋንዳ እድገት እንጅ በተጨባጭ በሕዝብ ጥቅምና ኑሮ ላይ ያመጣው ለውጥ አለመኖሩ የተረጋገጠ ነው። ቀድሞም ቢሆን ደካማ የነበረው ኢኮኖሚ  ዛሬ  በድርቅና ረሃብ፣እንዲሁም በዓለም አቀፉ ገበያ መቀነስ ምክንያት ቀንሷል ተብሏል። ወያኔ በፕሮፓጋንዳ በሚያስፋፋው ዕድገት ስም ከ17 ቢሊዮን ዶላር በላይ በአገሪቱ ስም መበደሩና የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሊሸከምው የማይችል ብድር መውሰዱ የኢኮኖሚው ባዶነት የሚያሳይ መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በአየር ንብረት  መዛባትና እንዲሁም በወያኔ አስከፊ አገዛዝ ምክንያት  በኢትዮጵያ የተንሰራፋው ድርቅና ረሃብ እያየለ ሄዶ ከወር ወደ ወር፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተረጅው ቁጥር እየጨመረና የአደጋው አስጊነት ይበልጥ እየሰፋ መምጣቱን የተመድ የሰብዓዊ ዕርዳታ አገልግሎት ቢሮ አስታውቋል። እንደ ተመድ ከሆነ በኢትዮጵያ አሁን የዕርዳታ ፈላጊው ቁጥር ወደ 20 ሚሊዮን መጠጋቱና ይህ አሀዝ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት አንድ አምስተኛውን የሚያጠቃልል መሆኑን ገልጿል። በረሃብና በድርቅ የተጎዱት አካባቢዎች ከ186 ወደ 219 ክፍ ያሉ ሲሆን ተረጅዎችም በከፋ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን በአንዳንድ አካባቢ ስደት መጀመሩና በዚህ ከቀጠለ የረሃብ አደጋ ዕልቂትን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመሆን በድርቅና በረሃብ ለተጎዱ ኢትጵያውያንና በጦርነት ለተጎዱ ሶርያውያን 2.2 ሚሊዮን ዕርዳታ እየተማጸኑ ሲሆን 480 ሚሊዮን ዶላር በድርቁና በረሃንብ ሳቢያ ጤንነታቸው ለተዛባ ኢትዮጵያውያንና በጦርነት ለተጎዳ ሶርያውያን ይውላል ተብሏል። የወያኔ ባለስልጣኖች  በወደብ የተከማቸ የእርዳታ እህል ለማንሳት ከመረባረብ ይልቅ በረሃብተኞች ህይወት ቁማር እየተጫወቱ መሆናቸው እየተጋለጠ ነው ተብሏል 

Ø ላለፉት ሶስት ዓመታት በወያኔ ፖሊሶች በግፍ ተይዞ በፈጠራ ወንጀል ተከሶ ወደ ወያኔው ፍርድ ቤት ይመላለስ የነበረው የሙስሊሞች ጉዳይ ጋዜጣ ማኔጅንግ ዲሬክተር ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ በትናንትናው ዕለት ሚያዚያ 5 ቀን 2008 ዓም.ከእስር መፈታቱ ታውቋል። ጋዜጠኛ ስለሞን ከበደ ለጋዜጠኛነት ሙያው ታማኝ በመሆኑና የጋዜጠኛነት ምግባሩን በተግባር በማሳየቱ በወያኔ ካድሬዎች ጥርስ ተነክሶበት ቆይቶ እንደነበርና ከሶስት ዓመት በፊት በፈጠራ ወንጀል ታስሮ ሰቆቃ ሲካሄድበት መቆየቱ ይታወሳል።  ልዮ ልዮ የጋዘጠኛ መብት አስከባሪና ተከራካሪ ድርጅቶች  ጋዜጠኛው በነጻ እንዲፈታ ሲወተውቱና ሲጠይቁ እንደነብረ ይታወቃል። የወያኔው የፖሊቲካ ፍርድ ቤት ጋዘጠኛ ሰለሞን ከበደን ሊያስቀጣውና ሊያሳስረው የሚችል ምንም ጥፋት ባለማግኘቱና ተጽእኖውና ግፊቱ ስለበረታ ከእስር ለመፈታት ተገደዱ እንጅ ዛሬም በወያኔ ወህኒ ቤት ውስጥ የጋዘጠኛነት ሙያቸውን በማክበራቸውና ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ብቻ በእስር የሚማቅቁ ጋዜጠኞች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን በግፍ ለታሰሩ ጋዜጠኞችና ዜጎች ሁሉ ድምጽ ማሰማት የማይታለፍ የአገር ወዳድ ዜጋ ግዴታ ነው ነው የሚሉ በርካታ ናቸው።

Ø ከሚያዚያ 8 እስከ ሚያዚያ 9 2008 ዓም. ድረስ በባህር ዳር ከተማ የሚካሄደውን አምስተኛ የጣና ፎረም ስብሰባን ምክንያት በማድረገ የባህር ዳር ከተማ በከፍተኛ ወታደራዊና የደህንነት ጥበቃ ስር መውደቋ ታውቋል። የወያኔ ደህንነት አባላት በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ የእንግዳ መቀበያና የመኝታ አገልግሎት መስጭያ ቤቶች እየዞሩ ማናቸውንም ፀጉረ ልውጥ ሰው አገልግሎት በፈለገ ጊዜ አስፈላጊውን መረጃ መያዝ ግዴታቸው እንደሆነና ለወያኔ ፖሊስም ማሳወቅ እንዳለባቸው ትዕዛዝ መስጠታቸው ታውቋል። በዚህ የጣና ፎረም ጉባዔ ላይ በሥልጣን ላይ ያሉ አምባገነን የአፍሪካ መሪዎችና ከስልጣን የወረዱ ፕሬዚዳንቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለባህርዳር ደህንነት ጥበቃ የወያኔ ቡድን መሪዎች ዘርን የተንተራሰ ምርጫ ማካሄዳቸውና ጠቅም ያለ አበል የሚከፈልበት በመሆኑ የትግራይ ተወላጆችን ማሰማራታቸው ቀደም ሲል መዘገባችን ይታወሳል
Ø ዛሬ ሐሙስ ሚያዚያ 5 ቀን 2008 ዓ.ም በጃፓን ኩማሞቶ በሚባለው አካባቢ መጠኑ 6.4 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰ መሆኑን የጃፓን የሜትሮሎጂ መስሪያ ቤት ገልጿል። የመሬት መንቀጥቀጡ ያደረሰው ጉዳት እስካሁን ባይገልጸም የሱናሚ ስጋት እንደሌለ ተገልጿል። ባለፈው እሁድ በደቡብ እስያ መጠኑ 6.6 የሚደረስ የመሬት መንቀጥቀጥ ደርሶ በህንድ በፓኪስታን እና በአፍጋኒስታን ህንጻዎችን መጉዳቱና  በተወሰኑ ሰዎች ላይም የአካል ጉዳት ማድረሱ የሚታወስ ሲሆን እንዲሁም ረቡዕ ሚያዚያ 5 ቀን መጠኑ 6.9 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ በሰሜን ሚያንማር (በርማ) የደረሰ መሆኑ ተዘግቧል።   
Ø በሰሜን ናይጄሪያ ቺቦክ ከተባለችው ከተማ 276 የሚሆኑ በትምህርት ቤት ውስጥ የነበሩ ልጃገረዶች ቦኮ ሃራም በተባለው አሸባሪ ቡድን ተጠልፈው ከተወሰዱ ሁለት ዓመት ሆናቸው ተባለ። ባለፈው ታኅሳስ ወር በተደራዳሪዎች አማካይነት ከቦኮ ሃራም ተገኘ ከሚባለውና የሲ ኤን ኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ካሳየው የቪዲዮ ቅጅ በርከት ያሉት ልጃገረዶች በህይወት መኖራቸው ታውቋል። ረቡዕ ሚያዚያ 5 ቀን 2008 ዓም ሲ ኤን ኤን ያሳየው ቪዲዮ ተቀረጸ የተባለው ታኅሳስ 15   ቀን 2008 ዓ.ም. በፈረጆቹ የገና በዓል ዕለት ሲሆን ከተጠለፉት ልጃገረዶች መካከል 15 ቱ በቪዲዮ ላይ ታይተዋል። ቪዲዮን የተመለከቱት አንዳንድ እናቶችና በዚያን ወቅት ያመለጡና ጓደኞቻችው የተመሰቃቀለ ስሜት ያደረባቸው መሆኑንና  በአንድ በኩል ልጆቹ በህይወት መኖራቸው ሲያስደስታቸው በሌላ በኩል ያሉበት ሁኔታ በጣም እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። ቦኮ ሃራም የተባለው አሸባሪ ድርጅት ለዓመታት ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ የቆየ ቢሆንም ልጃገረዶችን በጅምላ ጠልፎ ሲወስድ በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ውግዘት የደረሰበት  መሆኑ ይታወሳል፡፤ በወቅቱ የነበረው የናይጄሪው የሚስተር ጉድላክ ጆናታን መንግስት በመጀመሪያ ልጃገረዶቹ መጠለፋቸውን ቢክድም በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ግፊት ለመቀበል ተገዷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ልጆቹን ለማስፈታት  በድርድርም ሆነ በሌላ መልክ ጥረት ቢደረግም እስካሁን የተገኘ መፍትሄ እንደሌለ ታውቋል።  ባለፈው ሳምንት የናይጄሪያ ወታደራዊ ተቋም ቦኮ ሃራም ከሚቆጣጠራቸው ቦታዎች 11698 ሰላማዊ ሰዎችን ነጻ ማውጣቱን ቢገልጽም ነጻ ወጡ የተባሉት ሰዎች ከቺቦክ የተያዙ ልጃገረዶችን አያካትቱም። ላለፉት ሁለት ዓመታት በቺቦክና በአካባቢው ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ምክንያት ከ20 ሺ በላይ ህጻናት የትምህርት ዕድል ተነፍገው ይገኛሉ።

Ø በብሩንዲ በጸጥታ ኃይሎች ተይዘው የሚወሰዱ ሰዎች መዳረሻቸው የሚጠፋ መሆኑ ተነገረ። የመንግስቱ ተጻራሪ ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ተወሰደው ከታሰሩ የሚጠብቃቸው በእስር ቤት በምርመራ መሰቃየትና ሞት ብቻ መሆኑን በርካታ ሰዎች እየተናገሩ ይገኛሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቤታቸው፤ከስራ ቦታቸው እና ከሌሎች ቦታዎች በጸጥታ ኃይሎች ታፍነው የሚወሰዱና መዳረሻቸው የሚጠፋ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን ቤተሰቦቻቸውና ወገኖቻቸው ያሉበትን ለማወቅ በርካታ ገንዘብ በጉቦ መልክ እንዲከፍሉ እየተደረገ መሆኑን ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች እየተናገሩ ይገኛሉ። አይ ብሩንዲ የተባለ በህቡዕ የተቋቋመ የኢንተርኔት ቡድን በጸጥታ ኃይሎች ተጠልፈው መዳረሻቸው የጠፉትን ሰዎች ስም እያሰበሰበ ሲሆን እስካሁን በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውና የጠፉትን ሰዎች ለማግኘት የሚከፈለው ጉቦ  ከ250 ዶላር እስከ 2500 ዶላር መድረሱን ገልጾ ጉዳዩን ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እያጋለጠ እንደሆነ አስታውቋል።  የብሩንዲ መንግስት አፈናውን ይካድ እንጅ ጸጥታውን ለማረጋጋት ማናቸውንም ዓይነት እርምጃ እንዲወስዱ ለጸጥታ ኃይሎች መመሪያ መስጠቱ ይታወቃል። በቅርቡ በዋናው ከተማ በቡጁምቡራ  ሙሳጋና ያካቢጋ በተባሉ ቀበሌዎች መሳሪያ ለማስፈታት የጸጥታ ኃይሎች የሚያካሄዱትን አሰሳ ለማምለጥ የመንደሮቹ ነዋሪዎች አብዛኞቹ ቤት ንብረታቸውን ጥለው በመሰዳዳቸው የተሰደዱትን ዜጎች ቁጥር ከ250 ሺ በላይ ያደረሰው መሆኑ ተገልጿል።
Ø ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 6 ቀን 2008 ዓም. ከፍተኛ የአውሮፓ ህብረት ቡድን ሊቢያ መግባቱና ከሊቢያ አንድነት መንግስት አባሎች ጋር መነጋገሩ ተገልጿል። የፈረንሳይ አምባሰደር እንዲሁም የእንግሊዝ እና የስፔን ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በሊቢያ ወደብ በባህር ኃይል የጦር ሰፈር ውስጥ ከአንድነቱ መንግስት ባለስልጣኖች ጋር ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን የአውሮፓው ህብረት የሊቢያን የአንድነት መንግስት ለመርዳት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 4 ቀን የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተመሳሳይ ጉብኝት አድርገው እርዳታና ትብብር ለማድረግ ቃል መግባታቸውና ባጭር ጊዜ ውስጥ ጣሊያን ኤምባሲዋን በትሪፖሊ ልትከፍት እንደምትችል መናገራቸው ተገልጿል። ከጥቂት ቀናት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የሊቢያ የአንድነት መንግስት አካል ትሪፖሊ ገብቶ በወደቡ አካባቢ ከባህር ኃይል ጦር ሰፈር ውስጥ ስራዎችን እያካሄደ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከአንዳንድ ወገኖች ድጋፍ ቢሰጠውም በትሪፖሊ የሚገኘው ራሱን መንግስት ነኝ የሚለው ክፍልና እንዲሁም በምስራቅ ሊቢያ የሚገኘውና የዓለም አቀፍ እውቅናና አግኝቶ የነበረው ምክር ቤት አብዛኞቹ የአንድነት መንግስቱን እየተቃወሙ መሆናቸው   ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment