አመፅ የሚያነሳሳ ቪዲዮ ወይም ጽሑፍ ማስተላለፍ በወንጀል ያስቀጣል
የሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ እንደወረደ:
የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡ በወታደራዊ ወይም ለዓለም አቀፍ ግንኙነት ሲባል በተሰየመ የኮምፒዩተር ዳታ ላይ የወንጀል ጥፋት የተሰነዘረ እንደሆነ፣ ድርጊቱ ከ15 እስከ 25 ዓመታት ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ይገልጻል፡፡
ይህ ቅጣት የሚጣለው ለወታደራዊና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሲባል ጥብቅ ሚስጥር በተባለ የኮምፒዩተር መረጃን (ዳታ) ያለፈቃድ ያገኘ፣ በሕገወጥ መንገድ የጠለፈ፣ እንዲሁም በኮምፒዩተር ሥርዓት ላይ ጣልቃ የገባ እንደሆነና ድርጊቱ የተፈጸመው በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ወይም አገሪቱ በአሥጊ ሁኔታ ላይ በምትገኝበት ወቅት ከሆነ ነው፡፡
ማክሰኞ ሚያዚያ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፓርላማው የቀረበው የዚህ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ እንደሚያስረዳው፣ የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅን ማውጣት ያስፈለገው በአገሪቱ እየደረሱ ያሉ የኮምፒዩተር ወንጀሎች (የሳይበር ጥቃቶች) እና ተጋላጭነትን መሠረት በማድረግ ነው፡፡
የረቂቅ አዋጁ ክፍል ሁለት እንደሚያስረዳው ማንኛውም ሰው ሆነ ብሎ ያለፈቃድ ወይም ከተሰጠው ፈቃድ ውጪ ይፋዊ ያልሆነን የኮምፒዩተር ዳታ ወይም የዳታ ፕሮሰሲንግ አገልግሎት የጠለፈ እንደሆነ፣ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና ከ10,000 እስከ 50,000 ብር በሚደርስ መቀጮ ይጣልበታል፡፡
ጠለፋው የተካሄደው በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ ማለትም በወታደራዊ የዕዝ ቁጥጥር ሲስተሞች፣ የደኅንነት፣ የፍትሕና የፀጥታ ተቋማት ሚስጥራዊ ዳታዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የትራንስፖርት የኮምፒዩተር ሲስተሞች፣ መሠረታዊ የሕዝብ አገልግሎቶችና የመሳሰሉት ላይ ከሆነ ከ10 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና ከ50,000 እስከ 100,000 ብር እንደሚያስቀጣ ይገልጻል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ጠለፋ ማለት በኮሙዩኒኬሽን ሒደት ላይ ያለን የኮምፒዩተር ዳታ ወይም የዳታ ፕሮሰሲንግ አገልግሎት መከታተል፣ መቅዳት፣ ማዳመጥ፣ መውሰድ፣ ማየት፣ መቆጣጠር ወይም ሌላ ተመሳሳይ ድርጊት መሆኑን ያስረዳል፡፡
በሰዎች የነፃነትና ክብር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሚል ንዑስ ርዕስ በአንቀጽ 13 ላይ የኮምፒዩተር ሥርዓትን በመጠቀም በሚሠራጭ ጽሑፍ፣ ንግግር፣ ቪዲዮ ወይም ሥዕል አማካይነት በሌላ ሰው ወይም በተጐጂው ቤተሰቦች ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ያስፈራራ ወይም የዛተ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡
በሕዝብ ደኅንነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሚለው በረቂቁ አንቀጽ 14 ላይ፣ ‹‹ማንኛውም ሰው በኅብረተሰቡ መካከል የፍርኃት ስሜት፣ አመፅ፣ ሁከት፣ ወይም ግጭት እንዲፈጠር የሚያነሳሳ ጽሑፍ፣ ተንቀሳቃሽ ምሥል፣ ድምፅ ወይም ማንኛውም ሌላ ምሥል በኮምፒዩተር ሥርዓት አማካይነት ያሠራጨ እንደሆነ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ያስቀጣል፤›› ይላል፡፡
የ‹ስፓም› መልዕክቶችን ስለማሠራጨት በሚለው የረቂቁ አንቀጽ 15 ድንጋጌ መሠረት ማንኛውም ሰው ምርትን ወይም አገልግሎትን ለማስተዋወቅ ወይም ለሽያጭ ለማቅረብ፣ መልዕክቶችን በአንድ ጊዜ ወደ በርካታ ኢሜል አድራሻዎች ያሠራጨ እንደሆነ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት መቀጮ ያስቀጣል፡፡ ወንጀሉ ከባድ በሆነ ጊዜ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከ50,000 ብር በማይበልጥ መቀጮ ያስቀጣል፡፡ ረቂቁን የተመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዝርዝር ዕይታ ለሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡
ሰሞኑን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለፓርላማ ያቀረቡት የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ከውጭ አገሮች በተሰነዘረ የኮምፒዩተር ጥቃት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የፌዴራል መንግሥት የዳታ ማዕከል አካል የሆነው የወረዳ ኔት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ይህንንም ጥቃት ዶ/ር ደብረ ጽዮን በኦሮሚያ ከተቀሰቀሰው አመፅ ጋር በማገናኘት ለማቀጣጠል ያቀዱ የሰነዘሩት መሆኑን፣ ነገር ግን በመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲና በሌሎች ባለድርሻ አካላት በቁጥጥር ሥር መዋሉን መናገራቸውንም መዘገባችን አይዘነጋም፡
No comments:
Post a Comment