በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ የሶሻሊስት ዴሞክራት ጥምረት አባላት የልዑካን ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ በዴሞክራሲያዊ ጉዳዮችና በመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ላይ ሲወያዩ፣ በፖለቲካ ምኅዳር ዙሪያ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም አነጋግረዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ መሪ ጂያኒ ፒቴላ ይህን ያስታወቁት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ካካሄዱ በኋላ በአውሮፓ ኅብረት ዋና ጽሕፈት ቤት መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር የተደረገው ውይይት አንድ ሰዓት ያህል መፍጀቱንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ ከአራት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ጠቁመው፣ ከፓርቲዎቹ ተወካዮች የተቃውሞ ሰነድ እንደቀረበላቸውም አስታውቀዋል፡፡
‹‹ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ባደረግነው ውይይት መንግሥትን በፅኑ የሚተቹ አስተያየቶችን አድምጠናል፡፡ በተለይም ደግሞ የምርጫ 2007 ውጤት ሕገወጥ መሆኑን ገልጸውልናል፤›› በማለት ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ስላደረጉት ውይይት ይዘት ጠቁመዋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት በቅርቡ በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ጨምሮ የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የሕገወጥ ሰዎች ዝውውርና የዴሞክራሲ ባህል መዳበር የውይይት አጀንዳዎች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
‹‹ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴሞክራሲን፣ የዜጎችን ነፃነትንና የሐሳብ ብዙኃነትን በተመለከተ መንግሥታቸው የተጠናከሩ ሥራዎችን መሥራት እንዳለበት አስረድቻለሁ፤›› ሲሉ የልዑካን ቡድኑ መሪ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽም በጎ እንደሆነ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥታቸው እየሠራ እንደሆነ እንዳስረዷቸውም ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ በቅርቡ ባወጣው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ላይ በኦሮሚያ የተከሰተውን አለመረጋጋት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ራፖርተር ምርመራ እንዲያካሂድ መጠየቁ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የዚህ ገለልተኛ አጣሪ ቡድንን የማሰማራት ዕቅድ ከምን ደርሷል? ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በዚህ ጉዳይ ተወያይታችኋል ወይ? ተብሎ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ጉዳዩ በውይይቱ ወቅት አልተነሳም ብለዋል፡፡
የኅብረቱ ፓርላማ ከ97ቱ ምርጫ ጀምሮ ጠንካራ ትችቶችን ያዘሉ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቦች ያቀርባል፡፡ ነገር ግን የውሳኔ ሐሳቦቹ ውጤት ምንድነው ለሚለው ጥያቄ ደግሞ፣ ‹‹በተደጋጋሚ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቦችን እናወጣለን፡፡ በቅርቡ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ካወጣን በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጉዳዩን በአንክሮ እንደተከታተሉት እናውቃለን፡፡ ይህ አንድ ውጤት ነው፡፡ ነገሩ ሁልጊዜ የሚነሳ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment