ፕሮፌሰር ባዬ ይማም
ለአፍታ ያክል ቆም ብለን እጅግ ከመዘውተሩ የተነሳ እየቸከ የመጣውን “የአማራ የበላይነት” ሐተታ ቅቡልነት በታሪካዊ ሃቆች ማንጸሪያነት ስንመርምር፤ አስቀድሞ የበላዮቹ አማሮች እነማን ናቸው? በዚህ ቡድን ውስጥ አባልነት እንዴት ይገለጣል? የአማራ ባህል ምንድነው? ባህል ሌሎች ቅሬታዎችንና በደሎችን መሸፈኛ ትዕምርት ቃል ነውን? ወይንስ ባህል አንድ ህዝብ በሌላው ላይ የበላይ መሆኑን የሚያመላክት ቃል ነውን? በደቡብ የግዛት መስፋፋት ስለተደረገባቸው አካባቢዎች በጅምላ እንደሚነገረው በስልጣን ላይ የነበረው ሰው ሁሉ አማራ ነው ብሎ ማስረገጥና ማረጋገጥ ይቻላልን? የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች በአእምሮአችን ያጭራሉ፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት
መጣጣርም ስለአማራ ትክክለኛውን ታሪካዊ እውነት ለመግለጥና ለመረዳት ያግዛል፡፡
ብዙ ጊዜ “የምኒልክ ታሪካዊ ድራማ መሪ ተዋንያንና ተጠቃሚዎች በዋነኛነት አማሮች” እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ አገላለጽ በእርግጥ ብዙሃኑ አማራ በጥቂቱ እንኳን ቢሆን ስማቸው የተለጠፈበት የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ስርዓት ተጠቃሚዎች ናቸው ማለት ይሆንን? በዚህ አውድ ውስጥስ አማራ በትክክል ማንን ያመለክታል? ጎጃሜዎችን፣ ጎንደሬዎችን፣ ወሎየዎችን ወይስ የሸዋን ሰዎች?
የአማራ መንግስት በሚሉት ስርዓት ውስጥ ሸዌ አማሮች አቢይ ተጠቃሚዎች ተደርገው እንደሚታዩ የብሄረተኞችን ጽሁፎች ያገላበጠ አንባቢ ሁሉ አያጣውም፡፡ ይህ ሲባልስ ብዙሃኑ የሸዋ አማራ የጥቅመ ብዙው ገዥ መደብ አባል ነው ማለት ይሆንን? በየትኛውም መንገድ አልነበረም፡፡
ሌላው ቀርቶ በአብዛኛው የመንግስት አመራር መዋቅር ተሹመው፣ አብዛኛውን የኢኮኖሚ ምንጮች ተቆጣጥረው፣ ብዙውን የአገሪቱን የግዛት ክልሎች ይገዙ የነበሩ፣ በደቡብ አውራጃዎች ሰፋፊ ሁዳዶች የነበሯቸውና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸው አዲስ አበባን ማዕከል አድርገው የመሰረቱ ነበሩ ተብሎ ቢታሰብ እንኳ የሸዋ መኳንንቶች ከአማራ ህዝብ እጅግ በጣም ጥቂቱን እጅ (አንድ መቶኛ) እንኳን የሚሸፍኑ አልነበሩም፡፡
በተቃራኒው ብዙሃኑ የሸዋ አማራ በድህነት የሚኖር ስልጣን አልባና እንደማንኛውም ቡድን በስርዓቱ የተመዘበረ ነበር፡፡ እንዲያውም “የሸዋ አማራ” በአንዳንድ ሁኔታዎች በደቡባዊው የሃገሪቱ ክፍል “ተጨቋኝ ከነበሩት ህዝቦች” እጅግ የከፋ ህይወት ይመራ እንደነበር የታሪክ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
እንቆቅልሽ የሚሆነው ከችግርና ከዘራፊዎች ጋር እየተናነቁ ህይወታቸውን ባቆዩ ስለምን ጎጃም፣ ጎንደር፣ ሸዋና ወሎ ቅኝ ገዥዎችና ጨቋኞች ተደርገው በጅምላ ተፈረጁ ነው፡፡ ይልቁንም እጅግ በርካታ የሆነውን የአማራ አርሶ አደር ቅኝ ገዥ አድርገው የሚያቀርቡት ይዞታችንን አጥተናል ከሚሉ ብሄረተኞች ርካሽ ወዳጅነትን ለመሸመት የሚሹ ፀረ አማራ አቋም ያላቸው ጸሃፊዎች ናቸው፡፡
አማራ ሌሎች ህዝቦችን ቅኝ ገዝቷል የሚል የሃሰት አሉባልታቸውን ቢያናፍሱም የስርዓቱ ተጠቃሚ አድርገው በሚከሱትና በሚወቅሱት አብዛኛው የአማራ አርሶ አደር ቀዬ የሚታየው ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እውነታ ፍጹም የተለየ ነው፡፡ በአካባቢው የተካሄደው የግምገማ ሪፖርትም እንደሚያመለክተው የገጠር ልማትን በተመለከተ የተሻለ እድገት አይታይም፡፡ ለምሳሌ በአማራ አካባቢ በሸዋ መንዝና ግሼ፣ ተጉለትና ቡልጋ እና መርሃቤቴ በትምህርት፣ በመንገድ ልማት፣ በጤና ማዕከላት ወዘተ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በባሰ እጅግ ኋላ ቀር ናቸው፡፡
የአማራ ቅኝ ገዥነት ፅንሥ ሀሳብ አቀንቃኞች ደጋግመው ወደሚያናፍሱት “የአማራ የባህል የበላይነት ወይም ጭቆና” ትኩረታችንን ስናዞርም እውነታው የተለየ መልክ አይኖረውም፡፡ “የባህል የበላይነት” የሚለው አገላለጽ ለመሆኑ በተለይ የባህሉ “አስፋፊዎች” ራሳቸው የህዝቦችና የባህሎች ውህደት ውጤት በሆኑበት ሁኔታ ከሌሎች ያልተቀየጠ የአንድ ነገድ ባህል ሊባል የሚችል ንጹህ ባህል አለን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የአማራ ባህልስ ለሌሎች ግንኙነትና ልውውጥ ላደረገባቸው ባህሎች መጥፋትና መዋጥ ስጋት ሆነዋልን? ይህ ሁኔታስ በደቡብ ባሉት ልዩ ልዩ ባህሎች ላይ ተንጸባርቋልን? ለመሆኑ የሌሎች ባህሎች ተጽዕኖ የማይጋባበት ምንም ሳይለወጥ በነባር መልኩና ይዞታው ሊኖር የሚችል ባህልስ አለን?
አስመሮም ለገሰ “የባህል ልውውጥ ሂደት አንድ ገጽታና መልክ ያለው ስዕል ተደርጎ አይታይም፣ ለምሳሌ የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች አማራ ሆኑ ብሎ ከማጠቃለል፣ ይልቁንስ ሁኔታው ውስብስብና አያሌ የባህል ቅርጾች በሚያደርጉት የእርስ በእርስ መስተጋብር ውስጥ ፍጹም አዲስ ባህል የሚወለድበት ሂደት ነው” በማለት ይገልጻል ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም፣ ክላፓም “የአማራ ባህል የነገደ-ብዙ ባህል እምብርት ነው” ማለቱም በረጅሙ የአገር-ብሄር ምስረታ ሂደት በህዝቦችና በባህሎች መካከል በተደረጉ የሃሳብ፣ የልምዶች፣ የሸቀጦች ወዘተ ልውውጥ ሂደትና አብሮ መኖር ውስጥ የተፈጠረውን የባህሎች መዛነቅ መግለጹ ነው፡፡
ከእነዚህ ሁኔታዎች ስንነሳም ‹‹የአማራ የበላይነት›› የሚለው አተያይ በታሪክ እውነታና ሃቅ ያልተመሰረተ ምናባዊ ልቦለድና የፈጠራ ተረታ ተረት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ይህ ተረት አንድም አፍራሽ በሆነ መንገድ የኢትዮጵያን ታሪክ በአውሮፓ ታሪክ መነጽር ለመመልከት ከመጣጣር፣ ያለበለዚያም ይሁነኝ ብሎ የታሪክ ሃቆችን በመበረዝና በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም የፖለቲካ አጀንዳን ከግብ ለማድረስ ከሚደረግ ጥረት የመነጨ ነው፡፡
እውነቱ መገለጽ ካለበት ደግሞ የአማራ ማህበረሰብ በቅኝ ግዛት ፅንሥ ሀሳብ አቀንቃኞችና በጀሌዎቻቸው ከተለጠፈበት መጥፎ ገጽታ በተጻራሪ ጠንካራ ሰራተኛ፣ ሰላም ወዳድ፣ ተባባሪና ታጋሽ ህብረተሰብ ነው፡፡ ቅኝ ገዥ ሆኖም አያውቅም፣ የበደላቸው ወገኖች ስለሌለም በጸጸት የሚተርከው የቅኝ ገዥነት ንስሃ የለውም፡፡
ስለዚህም የአማራ ህዝብ ያልስራው እና በውሸት የተቀባው የታሪክ ጥላሸት ሊነጻ፣ ያለ ግብሩ የተጫነበት የገዥነት አመል አለው የሚል ውግዘት ሊረሳና ሊቆም፣ በምትኩም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያለው ትክክለኛ ቦታና ያበረከታቸው ታላላቅ ተግባራት ሊነገሩለት ይገባል፡፡
No comments:
Post a Comment