ሚያዚያ 05 ቀን 2008 ዓ.ም.ዜና (April 13, 2016 NEWS)
#ዜጎች የኮምፒውተር ወንጀል ፈጽማችኋል ተብለው ሊከሰሱ ነው
#በሻሽመኔ አንድ አዳራሽ በመድርመሱ አስር ሰዎች ህይወታቸው አጡ
#አሜሪካና ወያኔ በወታደራዊ ጉዳዮች ስምምነት አደረጉ
#በደቡብ ሱዳን ሁለት የእርዳታ ሰጭ ድርጅት አባላት ተገደሉ፤ የሪክ ማቻር ምክትል ጁባ ገቡ
#በማሊ ሶስት የፈረንሳይ ወታደሮች መንገድ ላይ በተቀበረ ፈንጅ ሞቱ
#ሶማሊያ ውስጥ 12 የአልሸባብ አባላት በሰው አልባ መንኮራኩር ተገደሉ ተባለ
#በሰሜን ናይጄሪያ በግፍ ተገድለው በጅምላ ተቀብረዋል የተባሉት የሺያ እምነት ተከታዮች ሁኔታ እንዲጣራ ተጠየቀ
ሚያዚያ 05 ቀን 2008 ዓ.ም.
Ø የወያኔ አገዛዝ ለስልጣኑ ተቀናቃኝ ይሆናሉ የሚሰጋባቸውን ጉዳዮች ሁሉ መቆጣጠርና እና መከታተል ሥራዬ ብሎ ከያዘ ወዲህ ሰሞኑን ደግሞ የኮምፒውተር ወንጀል ቅጣት በአዋጅ መልክ ህግ ሆኖ እንዲወጣ ጉዳዩን ለፓርላማ አቅርቧል። የመጣለትን ሁሉ በጭብጨባ ብቻ የሚቀበለው የወያኔ ፓርላማም ረቂቅ ህጉን ይቀበላዋል ተብሎ ይጠበቃል። የወያኔ መሪዎች የኮምፒወተር ረቂቅ ህግን ለማውጣት የተገደዱበት ምክንያት ተቃውሞና አመጽ ያቀዱ መልእክቶች ያለ ተጠያቂነት በብዛት ሲሰራጩ በመቆየታቸው ነው ተብሏል። በተጨማሪም በኮምፒውተር ደረጃ ወንጀል እየበረከተ መምጣቱም ለረቂቅ አዋጁ መውጣት ሌላው ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል። የወያኔው ረቂቅ አዋጅ የአገዛዙን ተቋማት በተለይም ወታደራዊ መረጃዎችን የሚገኙባችው የኮምፒውተር ፋይሎች እንዳይጠፉና እንዳይሰረቁ ልዩ ትኩረት ያደርጋል የተባለ ሲሆን ወያኔን ከስልጣን ለማባረር ይንቀስቃሳሉ የሚባሉ ቡድኖችና ግለስቦችን ለመቆጣጠርም ታስቦ ነው። በዚህ የኮምፒውተር ወንጀል የተከሰሰ ሰው ከ 15 እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት እንደሚጠብቀው ረቂቅ ህጉ ይደነግጋል።
Ø በደቡብ ኢትዮጵያ በሻሸመኔ ከተማ ቀድሞ መጸዳጃ ቤት የነበረ ቦታ ላይ የአምልኮት መፈጸሚያ አዳራሽ ተሰርቶ አዳራሹ በመደርመሱ አስር ሰዎች መሞታቸው ታወቀ። ይህ በአሌሉ ክፍለ ከተማ ቀበሌ አስር ውስጥ ያለው መጻዳጃ ቤት መቼ እንደተቆፈረና መቼ እንደተዘጋ ባይታወቅም ህያው የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን የሚባል የአምልኮ ማካሄጃ ቤት ከአንድ ዓመት በፊት መገንባቱ ታውቋል፡፤ አዳራሹ በሚደረመስበት ሰዓት አስራ ስምንት ሰዎች አምልኮ ይፈጽሙ የነበሩ ሲሆን በሕዝብና በነዋሪው ትብብር ስምንት ሰዎችን ሰባት ሜትር ጥልቀት ካለው ጉድጓ ሊያወጧቸው ተችሏል። አደጋው ሰኞ ሚያዚያ 3 ቀን 2008 ዓም መድረሱ ሲታወቅ በህይወት የተረፉትን ሰዎች ለማውጣት ለሳብት ሰዓታት ከፍተኛ ጥረት መደረጉ ታውቋል።
Ø አሜሪካና ወያኔ በሱማሊያ ጉዳይ ላይ ያተኮረ አንድ የትብብር ስምምነት መፈራርማቸውን የአሜሪካ መንግስት ባለሥልጣኖች አስታውቀዋል። ስምምነቱ በጸጥታና በመከላከያ ዙሪያ ሲሆን በአሜሪካ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት በአሜሪካ ጦር ኃይል የአፍሪካ ኮማንድ አዛዥ ጄኔራል ዴቪድ ሮድሪዚግ ሲሆኑ በወያኔ በኩል የወያኔው ኤታ ማጆር ሹም የተባለው የጦር አለቃ ሳሙራ ዩኒስና የወያኔ መከላከያ ሚኒስትር ተብዬ ስራጅ ፈርጌሳ ናቸው። እአአ በ2007 ዓ.ም. በአሜሪካ ቡራኬ ወያኔ ሱማሊያ ውስጥ ወረራ ማካሄዱ ይታወሳል። አልሸባብን ለመዋጋት በሚል አሜሪካ ለወያኔ ጋር ከፍተኛ ወታደራዊ ትብብር ስትሰጥ መቆየቷ የሚታወቅ ሲሆን ድሮን ለተባለው አብራሪ አልባ መንኮራኩሮች ማረፊያና የጦር ስፈር በገሙጎፋ አርባ ምንጭ ከወያኔ ተችራ እንደነበርም ይታወቃል። አሜሪካ የጦር ሠፈሯን ከአርባ ምንጭ ነቅላ ከወጣች ወዲህ ከወያኔ ጋር አዲስ ወታድራዊና የጸጥታ ስምምነት ስትፈርም ይህ የመጀመሪው ነው።
Ø በደቡብ ሱዳን ሁለት የእርዳታ ሰጭ ድርጅት ሠራተኞች በታጣቂ ኃይሎች የተገደሉ መሆናቸው ታውቋል። ዳኒሽ ዲማይኒንግ ግሩፕ (Dannish Demining Group) ለሚባለው የቦምብ አምካኝ የሰብአዊ መብት ድርጅት ይሰሩ የነበሩት ሁለቱ ግለሰቦች የደቡብ ሱዳን ዜጎች ሲሆኑ ወደስራ ከሚሄዱበት መኪና በታጣቂዎች እንዲወርዱ ተገድደው በጥይት ተመተው የተገደሉ መሆናቸውን የዓይን እማኞች ገልጸዋል። እስካሁን ድረስ በደቡብ ሱዳን በታጣቂዎች የተገደሉ የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች አባላት 51 የደረሰ ሲሆን ግጭቱ እስከቀጠለ ድረስ ቁጥሩ ሊቀጥል እንደሚችል ተገምቷል፡፡
Ø በተያያዘ ዜና የደቡብ ሱዳን አማጽያን ኃይል ምክትል መሪ ሚስተር አልፍሬድ ላዱ ጎሬ በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ የገቡ መሆናቸው ተነግሯል። በተደረገው ስምምነት መሰረት የጸጥታውን ሁኔታ የሚያስከብር 1300 የሚሆኑ የአማጽያኑ ኃይል ወታደሮችና የጸጥታ ኃይሎች ቀደም ብለው ጁባ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን ዋና መሪ ሚስተር ሪክ ማቻርም በሚቀጥለው ሰኞ ጁባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የምክትል መሪው ጁባ መግባት በእርግጥም በአገሪቱ ላይ ሰላም እየሰፈነ ነው የሚለውን ግምት ከፍ አድርጎታል ተብሏል። ሚስተር ጎሬ ጁባ ሲገቡ በተናገሩት ቃል ከእንግዲህ ሰላም አይቀለበስም የሚል መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን 16 የአማጽያኑ ኃይል አባላት በመንግስት ኃይሎች መታሰራቸውንና ተደብድበው መለቀቃቸውን አውግዘዋል።
ከዚህ ሌላ አንድ የአፍሪካ ህብረት የመልክተኛ ቡድን በደቡብ ሱዳን የአንድነቱን የሽግግር መንግስት ለማጠናከር ጁባ የገባ መሆኑ ተገልጿል።
Ø በማሊ የታጠቁ ኃይሎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አሁንም ያልተዳከመ መሆኑ ተነግሯል። በቅርቡ በመንገድ ላይ በተቀበረ የፈንጅ አደጋ ሶስት የፈረንሳይ ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት የተገደሉ መሆናቸው የፈረንሳይ መንግስት ቃል አቀባይ ገልጿል፡፡ ሶስቱ ወታደሮች የተገደሉት በሰሜን ማሊ ሽብረተኞች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ወታድሮችን የጫኑ 60 ተሽከርካሪ ካሚዮኖች የሚገኙበት ኮንቮይ በሰሜን ማሊ ሲንቀሳቀስ ሟቾቹ የነበሩበት መኪና በፈንጅው በተመታበት ጊዜ ሲሆን ሌሎች ወታደሮችም የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ተነግሯል። ፈረንሳይ 3500 ወታደሮች በሰላም አስከባሪ ኃይል ስር በአምስት የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ያሰማራች ስትሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማሊ ውስጥ የተገደሉት የፈረንሳይ ወታደሮች ከአሁኑቹ ጋር ወደ ሰባት መድረሱ ተገልጿል።
Ø ሚያዚያ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በደቡብ ሱማሊያ ኪስማዮ በተባለው የወደብ ከተማ አሜሪካ በሰው አልባ መንኮራኩር አማካይነት ባካሄዳችው የአየር ጥቃት 12 የአልሸባብ አባላት መግደሏን ገልጻለች። የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋም የፔንታጎን ቃል አቀባይ በሰጠው መግለጫ የተገደሉት የአልሸባብ አባላት በአሜሪካ እና በሱማሌ መንግስት ወታደሮች ላይ አደጋ ለማድረስ ሲያቅዱ የነበሩ ናቸው ብሏል። በከተማዋ የሚኖሩ የአይን እማኞች በሰው አልባው መንኮራኩር ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው ከተገደሉት መካከል አብዛኞቹ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው ብለዋል።
Ø ባለፈው ታህሣስ ወር በሰሜን ናይጀሪያ 347 የሚሆኑ የሺያ ሙስሊም እምነት ተክታዮች በናይጄሪያ ወታደራዊ ኃይል አባላት በግፍ ከተገደሉ በኋላ በጅምላ መቃብር ውስጥ ተቀብረዋል በማለት አንድ የቀድሞ የአካቢው ባለስልጣን ለመርማሪ ቡድን የሰጡትን ቃል ተከትሎ ሰዎቹ ተቀብረውበታል የተባለው ቦታ ታጥሮ በጥበቃ ስር እንዲቆይና ምርመራ እንዲካሄድበት የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በመግለጫው ውስጥ በሰሜን ናይጄሪያ ውስጥ የሚገኘው የካዱኑ ግዛት የመንግስት ኃላፊዎች ሚስጥሩን ማውጣቸውን አድንቆ ወንጀለኞችን ወደ ፍርድ ለማምጣት እና የሚገባቸውን ቅጣት ለመበየን ገለልተኛ በሆነ ኃይል ጉዳዩ መመርመር አለበት ብሏል። በተያዙበት ጊዜ በደረሰባቸው ድብደባ እና እንግልት አይናችው ጠፍቷል የሚባሉት የእምነቱ ተከታዮች መሪም ባስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ ጠይቋል።
No comments:
Post a Comment