ሁለት አነስተኛ ድንኳኖች በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ ሐሩርና ንዳድ ለመከላከል ያስችሉ ዘንድ ተዘርግተዋል፡፡ በአንደኛው ድንኳን ውስጥ አራት ፍራሾች ተዘርግተው፣ ኢልኒኖ ባስከተለው ከፍተኛ ድርቅ የተነሳ የምግብ እጥረት የገጠማቸውን ሕፃናትና እናቶች ለመንከባከብ እንዲያስችሉ አንሶላ ለብሰው ተዘጋጅተዋል፡፡
በእነዚህ ድንኳኖች ውስጥ ደግሞ ‹‹ሴቭ ዘ ቺልድረን›› የሚል ጽሑፍ የተጻፈበት ቲሸርት የደረቡ የጤና ረዳቶች፣ ጤናቸው በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ ሕፃናትና እናቶችን አስተኝተው የጤና እንክብካቤ ያደርጋሉ፡፡ በተለይ ለሕፃናቱ ደግሞ አልሚ ምግብ ለመስጠት ወዲያ ወዲህ ይላሉ፡፡
ከድንኳኑ ፊት ለፊት በሁለት ቋሚና በአንድ አግዳሚ እንጨት ላይ ተንጠልጥሎ በተሰቀለ ሚዛን ላይ የሕፃናቱን ክብደት ለመለካት ደግሞ፣ ሌሎች የጤና ኬላው ሠራተኞች ተፍተፍ ይላሉ፡፡
ምንም እንኳን ሰዓቱ ገና ከማለዳው ለሦስት ሰዓት ሩብ ጉዳይ ቢሆንም፣ በአካባቢው የወጣው ፀሐይ አናት የሚበሳ የሚባለው ዓይነት ነው፡፡ ከተከሰተው ድርቅ ጋር ተደምሮ ገና በጠዋቱ በሥፍራው ያለው የፀሐይ ኃይልና የመወበቅ ስሜት ለመንቀሳቀስ እጅግ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡
በሥፍራው ያለው የአየር ሁኔታ በአጠቃላይ ዘንድሮ የተከሰተውን የድርቅ ሁኔታና የአየር መዛባት ገጽታ ምን እንደሚመስል ቋሚ ምስክር ከመሆኑም በላይ፣ የችግርና የእርዛቱን መጠን በጉልህ የሚያሳይ ጭምር ነው፡፡
በዚህ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ውስጥም ቢሆን የተዳከሙ እናቶች በእናትነት ፍቅርና እንስፍስፍ አንጀት እየተመሩ፣ በምግብ እጥረት ክፉኛ የተጎዱ ሕፃናት ልጆቻቸውን የመዳንና የመመገብ ተስፋ ወዳደረጉበት የጤና ኬላ ይዘው ይመጣሉ፡፡
ይህ ሁሉ የሚከናወነው በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከሚገኙና የዘንድሮው ድርቅ ክፉኛ ካጠቃቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው በሽንሌ ዞን ሥር በሚገኘው ፈዴቶ የጤና ኬላ ነው፡፡
የጤና ኬላው ሠራተኞችም ዜጎችን የማከም፣ እንዲሁም ለሕፃናት የሚሆን አልሚ ምግብ የማደል ሥራቸውን ተያይዘውታል፡፡ የአየር ሁኔታው ግን እጅግ በጣም ከባድ የሚባል ነው፡፡ ከላይ የፀሐይ ኃይል ከታች ደግሞ የመሬቱ ግለት አካባቢውን ለመኖር እጅግ በጣም አስቸጋሪ አድርገውታል፡፡
በጤና ኬላው የሚስተዋሉት በአብዛኛው ሕፃናትና እናቶች ናቸው፡፡ ድርቁ ባስከተለው የምግብ እጥረት የተነሳ ከተጎሳቆሉት ሕፃናት በተጨማሪ፣ በተለያዩ በሽታዎች የተጠቁ እናቶችና ሕፃናቶችም የጤና ኬላውን ይጎበኛሉ፡፡
በሳምንት ሁለት ቀን አጠቃላይ ሕክምና እንዲሁም አልሚ ምግብ ለማግኘት ወደ ሥፍራው የሚመጡት ሕፃናትና እናቶች በርካቶች ቢሆኑም፣ የጤና ኬላው አገልግሎት መስጠት የሚችለው 29 ለሚሆኑ አዳዲስ ታካሚዎችና ከሰባት እስከ አሥር ለሚደርሱ ክትትል ለሚያደርጉ ሕፃናትና እናቶች ነው፡፡
‹‹በአሁኑ ሰዓት የጤና ኬላው ሦስት መሠረታዊ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ እነዚህም አዳዲስ ታካሚዎችን መቀበል፣ ሕክምና የጀመሩትን መከታተልና የምክር አገልግሎት መስጠትን የተመለከቱ ናቸው፤›› በማለት ለሪፖርተር የገለጹት የፈዴቶ ጤና ጣቢያ የሴቭ ዘ ቺልድረን ሲኒየር ኦፊሰር የሆኑት አቶ አብዲዋሳ አህመድ ቃሲም ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም እዚህ ለሕክምና የሚመጡት ግለሰቦች የራሳቸው የሆነ ከብትና ንብረት እንደነበራቸው የሚጠቅሱት አቶ አብዲዋሳ፣ አሁን ግን በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ንብረታቸውን በማጣታቸው ለምግብ እጥረትና ለጤና መታወክ እንደተጋለጡ አመልክተዋል፡፡
‹‹ምንም እንኳን ወደ ጤና ኬላው ለሚመጡት ሕፃናት አልሚ ምግብ የማደል ችግር ባይኖርም፣ በአጠቃላይ በኅብረተሰቡ ውስጥ ግን የምግብ እጥረት ይስተዋላል፤›› በማለትም አክለው ያስረዳሉ፡፡
የዘንድሮ ድርቅ በከፍተኛ ሁኔታ ካጠቃቸው ክልሎች ውስጥ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አንዱ ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደሚገለጸው በኤልኒኖ ሳቢያ በተፈጠረው የአየር መዛባት ምክንያት በአካባቢው ላለፉት ሁለት ዓመታት ዝናብ ባለመዝነቡ ምክንያት ነው፡፡
የ65 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት አቶ ኤልቲሬ ሙሴባብ በሕይወት ዘመናቸው ካጋጠማቸው ሁሉ የከፋው ድርቅ ይህ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ወደ ሰማይ አንጋጠው ፈጣሪን በልመና ዝናቡን ደግሞ በተስፋ መጠባበቅ የዕለት ተዕለት ሥራቸው ከሆነ መሰነባበቱንም ተናግረዋል፡፡
‹‹በራሳችን የምንኖር የነበርን ሰዎች ባለፉት ሁለት ክረምቶች ዝናብ ባለመዝነቡ የተነሳ፣ ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት ለሚሰጥ የምግብ ዕርዳታ ጥገኛ ሆነናል፡፡ ምንም ዓይነት አማራጭ የለንም፡፡ ቁጭ ብለን የምንጠብቀው ከመንግሥት የሚሰጠንን ዕርዳታ ብቻ ነው፤›› በማለት በአካባቢው የደረሰውን አስከፊ ችግር በተሰበረ አንደበት ይገልጻሉ፡፡
በሕይወት ዘመናቸው አጋጥሟቸው የማያውቀውን ይህንን ድርቅ የአካባቢው ነዋሪዎች ስም እንዳወጡለት የጠቆሙት አቶ ኤልቲሬ፣ ‹‹የዘንድሮውን ድርቅ ስሙን ‹ሙልያ› ብለነዋል፡፡ ትርጉሙም ሁሉንም ንብረት ጠራርጎ የሚወስድ እንደማለት ነው፤›› በማለት የደረቀውንና የተሰነጣጠቀውን መሬት በከዘራቸው እየመቱ ገልጸዋል፡፡
በየንግግራቸው መካከል ለደቂቃዎች እረፍት እየወሰዱ በተስፋ ወደ ሰማይ የሚያንጋጥጡት አቶ ኤልቲሬ፣ ሁሉንም ጠራርጎ የወሰደባቸው ድርቅ የወሰደባቸውን እንዲመልስላቸው የሚማፀኑ ይመስላሉ፡፡
ሌላው በድርቁ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚገልጹት ደግሞ የ33 ዓመቷ ወይዘሮ ደሀቦ ናቸው፡፡ በደህናው ቀን በርካታ ግመሎች፣ ፍየሎችና አህዮች እንደነበራቸው በትዝታ ወደኋላ ተጉዘው የሚያስታውሱ ሲሆን፣ አሁን ከድርቁ መከሰት በኋላ ግን የቀሩዋቸው ሦስት ፍየሎችና አንድ አህያ ብቻ እንደሆኑ በሐዘን ይናገራሉ፡፡
‹‹ከአሁን በኋላ ሕይወት እንዴት እንደሚቀጠል የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ ከመንግሥትና ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች የተለያዩ ዕርዳታዎች ይደረጉልናል፡፡ ነገር ግን ዕርዳታዎቹ ምን ያህል ይወስዱናል? ያለቁብንን ከብቶችስ እንዴት መመለስ ይቻላል?›› በማለት እንባ ባቀረረ ዓይናቸው የሩቁን ተስፋ አልባ ጉዞ እየተመለከቱ በሐዘንና በመልስ አልባው ጥያቄያቸው ውስጥ ይሰጥማሉ፡፡
በሥፍራው የተገኙት አብዛኛዎቹ አርብቶ አደሮች በአብዛኛው ከብቶቻቸውን አጥተዋል፡፡ የሚላስ የሚቀመስ የላቸውም፡፡ በአጠቃላይ ቀጣይ የሕይወታቸው ዕጣ ፈንታ የተንጠለጠለው ከመንግሥትና ከለጋሽ አካላት በሚያገኙት ድጋፍ ላይ ብቻ ይመስላል፡፡
በከፍተኛ ሁኔታ የተራቆተው መሬት ከአሁን በኋላ ዝናቡ መዝነብ ቢጀምር እንኳን፣ በምን ያህል ጊዜ አገግሞ ለእንስሳት የሚሆን ግጦሽና ምርት መስጠት እንደሚጀምር መገመት ይከብዳል፡፡
የተለያዩ ሪፖርቶች እንደሚጠቀሙት በክልሉ በአብዛኛው በሚባል ሁኔታ እንስሳት ሞተዋል፡፡ ይህም ችግሩን የተወሳሰበ ያደርገዋል፡፡
የመንግሥትና የለጋሽ አገሮች ምላሽ
በመንግሥት ደረጃ እስካሁን ድረስ በድርቅ የተጎዱ 10.1 ሚሊዮን ዜጎች መኖራቸው ተገልጿል፡፡ ችግሩ ወደከፋ ደረጃ ከመሸጋገሩና የሰው ሕይወት ከመጥፋቱ በፊት፣ የመከላከል ሥራ ለማከናወንና ለተጎጂዎች አስፈላጊውን የምግብና የተለያዩ ዕርዳታ ለማድረግ እንዲቻል 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
ምንም እንኳን ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ድርቁን ለመከላከልና ለተጎጂዎች አስፈላጊውን ዕርዳታ ለማድረስ የመንግሥት ጥያቄ ካቀረበ በኋላ የተሰጠው ምላሽ አነስተኛ እንደሆነ መንግሥት በተደጋጋሚ ቢያስታውቅም፣ በራሱ አቅም ለችግሩ መፍትሔ እየሰጠ እንደሆነ ግን ይገልጻል፡፡
በእስካሁኑ ሒደት ለተጎጂዎች የምግብና ሌሎች ዕርዳታዎችን ለማድረግ ከሚያስፈልገው አጠቃላይ ገንዘብ ውስጥ የተሰበሰበው 51 በመቶ ብቻ መሆኑን በመጥቀስ፣ ዕርዳታው በሚፈለገው መጠን እንዳልተገኘ መንግሥት እየገለጸ ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት የምግብ ዋስትና ዘርፍ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ መሐመድ ጣሒር ‹‹በክልሉ የተከሰተው ድርቅ ከእኛ ቁጥጥርና ከአቅማችን በላይ ነው፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡ እስካሁን ድረስ ከፌዴራል መንግሥቱ የተደረገላቸው ድጋፍና ዕርዳታ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዕርዳታው አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለት ያሳስባሉ፡፡
በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ፣ የጉዳት ልክና መጠን ለመመልከት ወደ ሽንሌ ዞን ባድ ወደተባለ አካባቢ ተገኝተው ጉብኝት ያደረጉት የአውሮፓ ኅብረት አራት ኮሚሽነሮችም የጉዳዩን አስቸጋሪነት መረዳታቸውንና አስፈላጊውን ዕርዳታ መስጠት እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ዕርዳታ ለኢትዮጵያ ከሚለግሱ ተቋማት በግንባር ቀደምትነት የሚሠለፍ ሲሆን፣ በተከሰተው ድርቅም የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ኅብረቱ በድርቅ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ካደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ፣ የ122.5 ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም ኮሚሽነሮቹ በሥፍራው ለተሰበሰቡት ተጎጂዎች ይፋ አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከአንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺሕ በላይ በድርቁ የተጎዱ ዜጎች ሲኖሩ፣ በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉት ደግሞ ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንደሆኑ አቶ መሐመድ በሥፍራው ለተገኙት የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽነሮችና ለሌሎችም አስረድተዋል፡፡
‹‹በክልሉ በድርቁ ለተጎዱት ዜጎች ከፌዴራል መንግሥትና ከለጋሽ አካላት ከሚደረግልን ድጋፍና ዕርዳታ ለመስጠትና ጉዳቱን ለመቀነስ በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን የሚደረግልን ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤›› በማለት በሥፍራው ለተገኙት የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናትና ለኅብረቱ ኮሚሽነሮች ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
‹‹በየትኛው ዓለም ክልል የሚፈጠረው ችግር ኢትዮጵያን እንዳንመለከት አያግደንም፡፡ በመሆኑም ለኢትዮጵያውያን ተጎጂ ወገኖች ዕርዳታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፤›› በማለት የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ ዕርዳታና ቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ክሪቶስ ስታይላንዲስ ቃል ገብተዋል፡፡
ከአውሮፓ ኅብረት የተለገሰውን ድጋፍ አስመልክቶ በሥፍራው አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ፣ ‹‹ይህ አሁን የተደረገው ድጋፍ እስካሁን ባለው 51 በመቶ ቁጥር ላይ ይጨምራል፡፡ ይህ ማለት ግን ሙሉ በሙሉ የሚፈለገውን ገንዘብ አስገኝቷል ማለት አይደለም፡፡ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፤›› በማለት ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
‹‹አሁን እንደምንመለከተው የበልግ ዝናብ እየዘነበ ነው፡፡ ይህ ዝናብ በዋነኛነት ሊፈታ የሚችለው የውኃ እጥረትና የእንስሳት መኖ ችግርን ነው፡፡ ነገር ግን ከምግብ አቅርቦት አንፃር ያለውን ችግር በተመለከተ የግድ የበልግ አዝመራንም ስለሚጠብቅ የግዴታ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤›› በማለት የድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠልን አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም፣ ‹‹መንግሥት 499,536 ሜትሪክ ቶን ምግብ እየገዛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እስከ መስከረም የሚወስደን ነው፡፡ ስለዚህ የለጋሾች ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ግን ቀደም ብሎ የምግብ አቅርቦት ክፍተት እንዳይፈጠር ለማድረግ በጀት መድቦ የምግብ ግዢ እያከናወነ ነው፡፡ የተገዛው ምግብ እስኪገባ ድረስ ደግሞ ከመጠባበቂያ የምግብ ክምችት ወስዶ የዕርዳታ ምግብ ያሠራጫል፤›› በማለት በአሁን ወቅት እየተከናወነ ያለውን ሥራ አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን ሥፍራ ባለፈው ሳምንት የጎበኙት የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽነሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ አዲሷ የሴቭ ዘ ቺልድረን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የቀድሞዋ የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሄለን ቶርኒንግ ሽሚት ጭምር ናቸው፡፡
ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ በመንግሥትም ሆነ በለጋሽ አካላት እስካሁን የተሠራው ሥራ መልካም መሆኑን ጠቅሰው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በነዋሪዎች ‹‹ሙልያ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሁሉንም ሀብት ንብረት የጠራረገው ድርቅ ባስከተለው ጉዳት ሳቢያ በደረሰው ችግር፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች የፈጣሪንና የመንግሥትን ዕርዳታ እየጠበቁ ነገን አሻግረው ይመለከታሉ፡፡ ነገ ምን ይዞላቸው እንደሚመጣ በእርግጠኝነት መናገር የተሳናቸው እነዚህ የድርቅ ተጎጂዎች፣ የተሻለ ቀን እንዲመጣላቸው ፈጣሪን በፀሎት ይለምናሉ፡፡ የፀሎታቸው ምላሽ ምን እንደሚሆን ለከርሞው በሚኖረው የምርት ውጤት የሚለካ ይሆናል፡፡ እስከዚያው ድረስ ከመንግሥት በሚሠፈርላቸው ራሽን ኑሮን ይገፋሉ፡፡ ይህ እስከ መቼ እንደሚቀጥል ወይም መቼ እንደሚያቆም ለመተንበይም ሆነ ለመናገርም እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ነው የሚስተዋለው፡፡
No comments:
Post a Comment