Saturday, April 9, 2016

የፍኖተ ዴሞክራሲ ራድዮ አጫጭር ዜናዎች



ርዕሰ ዜና
·         የእስራኤል መንግስት ተጨማሪ ቤተእስራኤሎች ወደ እስራኤል እንዲገቡ ፈቀደ
·         በጂቡቲ ምርጫ እየተካሄደ ነው
·         በሊቢያ የአሲስ አባላት ቁጥር እየጨመረ መጣ ተባለ
·         የሴየራ ሊዮን ፕሬዚዳንት የውጭ ባለሀብቶችን ተማጸኑ
·         ሞሮኮ የውጭ ዜጎች ከሀገሯ አባረረች
መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም.
Ø ተጨማሪ የቤት እስራዔሎች ቤተሰቦች በዚህ አመት ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ሊመጡ ስለሚችሉበት ሁኔታ የእስራዔል ገዥ ፓርቲ ከአጋሮቹ ጋር ስምምነት የደረሰ መሆኑን ሐሙስ መጋቢት 29 ቀን ማምሻውን በሰጠው መግለጫ ገልጿል። በዚህ 1300 የሚሆኑት እንዲመጡ የተፈቀደ ሲሆን ወደፊት ቁጥሩ  ከዚህ በላይ ሊጨምር የሚችል መሆኑን ተገልጿል። ባለፈው ወር በእስራዔል አገር የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘመዶቻቸው ወደ እስራኤል እንዲመጡ በመጠየቅ ከፍተኛ ትዕየንተ ሕዝብ ማካሄዳቸው የሚታወስ ሲሆን የእስራዔል መንግስት ነገሩን ችላ በማለት ኢትዮጵያውያኑን  የፈቃዱን ውሳኔ ሲያስተላልፍ መቆየቱ ይታወሳል። ባለፉት ጥቂት ቀናት አንዳንድ የፓርላማ አባላት ባደረጉ ጥረትና እንዲሁም ተቃውሞውና አድማው የጋራ መንግስቱን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል መሆኑ ስለገባው  ገዥው ፓርቲ ሀሳቡን ቀይሮ ቤተእስራኤሎቹ ወደ እእስራኤል እንዲመጡ ፈቅዷል።
File PhotoFile Photo
Ø በጂቡቲ ዛሬ መጋቢት 30 ቀን 2008 ዓም  ጠቅላላ ምርጫ እየተካሄደ ሲሆን የጂቡቲው ፕሬዚዳንት አሸናፊ ሆነው እንድሚቀርቡ አስቀድሞ ታውቋል። ስድስት ተወዳዳሪዎች ለምርጫው ቢቀርቡም ላለፉት 17 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዚዳንት አሸናፊ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም በማለት ታዛቢዎች ይተቻሉ። ከተቃዋሚዎች ውስጥ የተወሰኑት በምርጫው ላለመሳተፍ የወሰኑ ሲሆን ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ደግሞ የፖሊሶች አፈና መጠናከሩንና የመገናኚያ ብዙሃን አድላዊነትን በመግለጽ ክስ እያሰሙ ይገኛሉ። ድምጹን የሚሰጠው  የጂቡቲ ሕዝብ ቁጥር አነስተኛ ነው የተባለ ሲሆን ፕሬዚዳንት ጉሌህ ከየመን የመጡ ስደተኞችን አስመዝገበው ድምጽ እንዲሰጡ እያደረጉ ነው ተብሏል። የተቃዋሚዎች መከፋፈል ጉሌህን ሊጠቅም ችሏል የሚሉ አልጠፉም። ከሶስት አመት በፊት የጉሌህ ተቃዋሚ የሆኑ ፓርቲዎች ትብብር ቢፈጥሩም ጉሌህ ተወዳድሮ ሊያሸንፍ የሚችል አንድ የጋራ ተወዳዳሪ ማውጣት ላይ ሊስማሙ አልቻሉም።  የምዕራብ አገሮች ጂቡቲ ውስጥ ባላቸው ጥቅም ምክንያት ስለምርጫው አስተያየት ሲሰጡ አይሰማም።
Ø በሊቢያ የአይሲስ አባላት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋም አዛዥ ተናገሩ። አዛዡ ላለፉት 12 እስከ 18 ወራት ባሉት ጊዚያት ወደሊቢያ የገቡት የአይሲስ አባላት ቁጥር ከ4 ሺ ወደ 6 ሺ ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸው አሸባሪዎቹ በብዛት ሊገቡ የቻሉት በአገሪቷ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ እና የጸጥታ አለመረጋጋት ተጠቅመው ነው ብለዋል። አብዛኞቹ ከውጭ የመጡ በመሆናቸውና አገር በቀል የሆኑ አባሎች አነሰተኛ በመሆናቸው እንደ ኢራክና እንደ ሶሪያ የተወሰነ ክልል ይዘው ለመቆጣጠር አይችሉም የሚል አስተያያት አዛዡ ጨምረው ገልጸዋል። በሊቢያ የሚገኙት ልዩ ልዩ የሚሊሺያ ቡድኖች በየቦታው ከአይሲስ ኃይሎች ጋር እየተጋጩ ስለሆነ በራሳቸው የሚጠናከሩበት ሁኔታ አነስተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
Ø የሴየራ ሊዮን ፕሬዚዳንት በአገራቸው የኢቦላ በሽታ የታደከመ መሆኑን ገልጸው የአገሪቷ ኢኮኖሚ ከወደቀበት ቦታ እንዲያንሰራራ ለማደረግ የውጭ አገር መዋእለ ንዋይ እንደሚያስፈልግ ተናገሩ። ከምዕራብ አፍሪካ አገሮች 11 ሺ ዜጎችን የገደለው የኢቦላ በሽታ የሲየራ ሊዮንን ኢኮኖሚ በተለይም የእርሻውን መስክ ክፉኛ ያጠቃው በመሆኑ የውጭ አገር ሀብታሞች ገንዘባቸውን በልዩ ልዩ የስራ መስክ ላይ በማዋል ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ እንዲያደርጉ ተማጽነዋል። ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ ቱርክ ውስጥ  በሚደረገው የእስላማውያን አገሮች አመታዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ተመሳሳይ ልመና የሚያቀርቡ መሆናችውን ገልጸዋል።
Ø የሞሮኮ መንግስት 8 የውጭ አገር ዜጎችን ከአገሩ ያባረረ መሆኑን ገለጸ። ተባረሩ የተባሉት ግለሰቦች ሁለት የፈረንሳይ አንድ የቤልጂክ እና አምስት የስፔይን ዜጎች ሲሆኑ ለመባረራቸው ምክንያት የሆነው በእስር ላይ ለሚገኙት የምዕራብ ሳህራ ዜጎች እርዳታና ትብብር አድርገዋል የሚል ነው። ከስድስት ዓመት በፊት ግድም ኢዚክ (Gdem Izik) በሚባለው በምዕራብ ሳህራ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የተቀጣጠለው ዓመጽ  ከሞሮኮ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት 11 ፖሊሶችና ሁለት ሰላማዊ ሰዎች መገደላችው አይዘነጋም። ፖሊስ  አመጹን ለማስቆም  ካምፑ እንዲፈርስ ያደረገ ሲሆን በርካታ ሰዎችን ወስዶ ማስሩ ይታወቃል። ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለው ድርጅት ባለፈው ህዳር ወር ተይዘው የሚገኙት የምዕራብ ሳህራ ዜጎች እንዲፈቱ መጠየቁ ይታወሳል።
Ø በዳርፉር አካባቢ የሽብር ተግባር ፈጽመዋል በሚል ክስ አንድ የሱዳን ፍርድ ቤት በ22 የደቡብ ሱዳን ዜጎች ላይ የሞት እና የእድሜ ልክ እስራት ቅጣት የበየነ መሆኑ ተገልጿል። ክስ የቀረበባቸው 22 ሰዎች ጀስቲስ ኤንድ ኢኩዋሊቲ ሙቭመንት የሚባለው የዳርፉ አማጽያን ቡድን አባላት ሲሆኑ ድርጅቱ ከሶስት አመት በፊት ከሱዳን መንግስት ጋር የእርቅ ስምምነት ፈርሞ የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ማቆሙ ይታወቃል። ባለፈው ጥር ወር 22 የደቡብ ሱዳን ዜጎች የአማጽያኑ ድርጅት አባል ሆነው መንቀሳቀሳቸው በመጋለጡ የውጭ አገር ዜጎች በመሆናችው ብቻ በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ ተደርጓል። ባሁኑ ጊዜ በደቡብ ሱዳን እና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት ከምንጊዜውም በላይ ዝቅተኛ ሆኖ የሚታይበት ሲሆን በሰዎቹ ላይ የተበየነው የፍርድ ውሳኔ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ይበልጥ ሊያሻክረው እንደሚችል ተገምቷል። የአለም አቀፉ ፍርድ ቤት በፕሬዚዳንት በሽር ላይ የወንጀለኛነት ክስ ለመመስረት ምክንያት በሆነው በዳርፉር ጦርነት 300 ሺ ሰው ያህል ህይወቱ ሲጠፋ ከ2.5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ ስደተኛ መሆኑ ይታወቃል
መጋቢት 29 ቀን 2008 ዓ.ም.
Ø በሱሉልታ ከተማ በወያኔ ወታደሮችና በከተማዋ ወጣቶች መካከል ፍጥጫና ውጥረት መፈጠሩ ታወቀ። ፍትጫው የተነሳው በሱልልታ ከተማ የሚገኝ አንድ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር መፈንዳቱን ተከትሎ የወያኔ ፖሊሶችና ጦር የከተማዋን ጥበቃ በማጠናከራቸው ሲሆን ወጣቶቹ ተቃውሞ በማሰማታቸው የወያኔ ፖሊስና ጦር ስትተኩስ ለመበተን የሞከሩ ሲሆን ከፍተኛ የዱላ ድብደባም መፈጸማቸው ታውቋል። የወጣቶቹ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሚደግበት ወቅት የወያኔ የንግድ ሸሪክ የሆነው የመሀመድ አላሙዲን ንብረት የሆኑ 3 መኪኖች ሲያልፉ በድንጋይ ተደብድበዋል።
Ø በሐረር ዓለማያ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች መኝታ ቤት ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ስለደረሰበት ተማሪዎች ትምሀርት አቋርጠው ወደ ቤተ ሰቦቻቸው ለመሄድ የተገደዱ መሆናቸው ከዓለማያ የመጣው መረጃ ያመለክታል። የእሳቱ አደጋ እንዴት እንደተቀሰቀሰና ለምን ሳይጠፋ ረጅም ሰዓት እንደቆየ የታወቀ ነገር ባይኖርም የዓለማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ነዋሪዎች ግን የወያኔ ደህንነት ኃይሎች የተማሪዎቹን መኝታ ክፍሎች ሆን ብለው በማቃጠል ያነጣጠሩባቸው ተማሪዎችንን መምህራንን በሽብረተኛነት ለመክሰስ በማሰብ ነው በማለት ይናገራሉ
Ø ከ10 አመት በፊት በጋምቤላ ከ400 በላይ አኙዋኮች ግድያን ተከትሎ ከወያኔ ጋር ሆድና ጀርባ በመሆን ከሀገር ወጥቶ በኖርዌይ በጥገኝነት ይኖር የነበረው ኦኬሎ አኳይ በወያኔው ፖለቲካ ፍርድ ቤት በሽብረተኛነት ጥፋተኛ ተብሎ የተፈረደበት ሲሆን ከሶስት ሳምንት በኋላ የቅጣቱ ብይን እንደሚሰጠው ተገልጿል። ኦኬሎ አኳይ በአኝዋኮች ፍጅት ወቅት የጋምቤላ ፕሬዚዳንት የነበረ ሲሆን በጋምቤላ የአኙዋኮችንና የኑዌር ግጭትን ወያኔዎች እንደቀሰቀሱት እና የአኙዋኮቹ ፍጅት በወቅቱ የወያኔ መሪ በነበረው በመለሰ ዜናዊ ትዕዛዝ እንደተፈጸመ ቀደም ሲል አስታውቆ የነበረ ሲሆን አሁንም በወያኔው የፖሊቲካ ፍርድ ቤት ደግሞታል። የወያኔ ወታደሮች 400 አኙዋኮችን ገድለው 60 ብቻ ነው የሞቱት የሚል ማስተባበያ ኦኬሎ እንዲሰጥ አስገድደውት እንደነበርና አዲሱ ለገሰ በረከት ስምኦንና ገብረአብ ባርናባስ የወያኔው ትዕዛዝ በማስፈጸም እጃቸው እንዳለበት ገልጿል። አኮሌ አኳይ ከዓመታት በፊት ወደ ደቡብ ሱዳን በሄደበት ወቅት የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣኖች ከወያኔ ደህንነት ጋር በመሳጠር ከጁባ ጠልፈውት ወደ አዲስ አበባ እንደመለሱትና በሽብረተኛነት ክስ እንደመሰረቱበት ይታወሳል።
Ø በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነትና ስልጣን ተቀምጠው እጅግ አስነዋሪ ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ የወያኔ ካባ ለባሽ ካድሬዎች ከስልጣናቸው መባረር መጀመራቸውና ዋና ጠባቂው አቡነ ማትያስም ምንም ማድረግ ባለመቻላቸው ለማባረር መገደዳቸው ታውቋል። የአቡነ ማትያስ ቀኝ እጅ የነበረውና የአዲስ አበባ ሀገር ስብከት ስራ አሲያጅ የነበረው የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ከየቤተክርስቲያኑና ገዳማቱ ያለውን ንብረት መዝረፉ ብቻ ሳይሆን ለልጁ መታከሚያ በሚል ሰበብ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ከቤተ ክርስቲያኗ ካዝና በመሰብሰቡ ከስልጣኑ የተባረረ ሲሆን በእርሱ ምትክ ሌላው ካባ ለባሽ ካድሬ ጎይቶም ያይኔ ተተክቷል። ከየማነ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ኃላፊዎችም ተባረዋል። የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ያሉ ማንኛውም ከፍተኛ ኃላፊነትና ስልጣን በትግራይ ተወላጆች ብቻ እንዲያዝ ባወጣው መመሪያ መሠርት በመንፈሳዊና ሐዋርያዊ ስራ በምትሰራው ቤት ክርስቲያን ውስጥ የዘር መድልዎን በማምጣት ቤተ ክርስትያኗን እያመሳት መሆኑ ምዕመናኑን ካህናቱ በጀመሩት ግፊት ካባ ለባሽ ካድሬዎች ቢነሱም ሌላ ዘረኛ ካባ ለባሽ መተካት ውጤት ስለሌለው ቤተ ክርስቲያኗን ከዘረኛ ካድሬ ቄስና መነኩሴ ማጽዳት የዛሬ ሰራ ነው የሚሉ ምዕመናን ብዙ ናቸው። 
Ø በአስመራ ከተማ በግድ ታፍሰው በካሚዮን ተጭነው ወደ ጦር ማሰልጠኛ ሲወሰዱ የነበሩ ወጣቶች ከተሳፈሩባቸው መኪናዎች ዘለው ለማምለጥ ሲሞክሩ በሻዕቢያ ወታደሮች በጥይት የተገደሉ መሆናቸው ታውቋል። የተገደሉትና እና ምን ያህል እንደሆኑ ለጊዜው ባይታወቅም ቁጥራቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል። በተጨማሪም  ካሚዮኖቹ የሚሄዱበትን መንገዶ በአውቶቡስ አማካይነት  ለመዝጋት ሙከራ ያደረጉ የወጣቶቹ ዘመዶችና ጓደኞች በሙሉ በጥይት የተገደሉ መሆናቸው ተነግሯል። የሻዕቢያ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ የሰጠው መግለጫ የለም። በሻዕቢያ ውስጥ የወታደራዊ አገልግሎት የጊዜ ወሰን የሌለው መሆኑ ሲታወቅ አብዛኛዎቹ እድሜ ልካቸውን ሲያገለግሉ የሚቆዩ መሆናቸውና  የኑሮው ሁኔታቸውም በጣም አሰቃቂ እንደሆነ ይነገራል። ይህ አሰቃቂ የኑሮ ሁኔታና የሻዕቢያን አፈና ለማምለጥ በርካታ ወጣቶች ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገሮች እና ወደ አውሮፓ መሰደዳቸው በየጊዜው የተገለጸ መሆኑ ሲታወቅ የሻዕቢያ አገዛዝ ከፍተኛ አፈናና ጭፍጨፋ ከሚያካሄዱ የአለም አገሮች ውስጥ ዋነኛው ነው በማለት የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ድምጻቸው በተደጋጋሚ ሲያሰሙ ቆይተዋል።
Ø በሊቢያ በፌስ ቡክ እና በሌሎች የማህበረሰባዊ መገናናዎች አማካይነት በድብቅ የሚካሄድ የመሳሪያ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ እየደራ መምጣቱን ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 29 ቀን ይሰራጫል የተባለ አንድ ጥናታዊ ዘገባ አመለከተ። ለአርባ ዓመት ሊቢያን ሲገዛ የቆየው የኮሎኔል ጋዳፊ አገዛዝ በየጊዜው ያከማቸው መሳሪያ አገዛዙ ሲወድቅ በተለያዩ አማጽያን እጅ የገባው መሳሪያ ዛሬ በጥቁር ገበያ በሰፊው እየተሸጠ መሆኑን ጥናቱ ይዘረዝራል። በፌስ ቡክ፣ በኢንስታግራም፣ በዋትስ አፕ፣ እና በቴሌግራም አማካይነት በብዛት እየተሸጡ ያሉት መሳሪያዎች እንደሽጉጥና ካላሽንኮቭ የመሳሰሉት የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች ሲሆኑ ለሽብርተኞች መገልገያ የሆኑ በትከሻ ላይ ሆነው የሚተኩሱ ጸረ አውሮፕላንና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችም የሚሸጡ መሆናቸውም ተጠቁሟል። አንድ ካላሽንኮፍ መሳሪያ እስከ 1800 ዶላር ሲያወጣ በተለይ የመጓጓዣ አውሮፕላንን ሊመታ የሚችል ጸረ አውሮፕላን መሳሪያ ደግሞ እስከ 62 ሺ የአሜሪካን ዶላር እንደሚሸጥ ዘገባው ይገልጻል። የመሳሪያ ሽያጮቹ የሚከናውኑት በአብዛኛው እንደ ትሪፖሊ፣ ቤንጋዚ እና ሳብራታ በመሳሰሉ ትላልቅ ከተሞች ሲሆን ንግዱ የሚካሄደው ወጣቶች በሆኑ የተለያዩ የሚሊሺያ አባላት መካከል መሆኑም ተድርሶበታል።  የፌስ ቡክ ቃል አቀባይ በሰጠው መግለጫ ይህን የመሰለ ንግድ በፌስ ቡክ አማካይነት መካሄዱ ወንጀል ገልጾ መረጃውን እየፌስ ቡክ አገግሎቱን እንዘጋዋለን ብሏል። የአውሮፓ ባለስልጣናትም ጉዳዩ ያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፤
    በተያያዘ ዜና ትሪፖሊን መሰረት አድርጎ ሲንቀሳቀስ  የነበረው የመንግስት አካል በትናንተናው ዕለት ደም መፋሰስን ለማስወገድ ከስልጣን ወርጃለሁ የሚል መግለጫ በፍርድ ሚኒስቴሩ አማካይነት መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን የዚሁ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሚስተር ካሊፋ ገውሊ  ደግሞ በድረ ገጻቸው ላይ ባወጡት መግለጫ ቀደም ብሎ የወጣውን መግለጫ መቃወማችውን ገልጸዋል። መግለጫ  ማንም ሚኒስቴር ሆነ ሌላ ኃላፊነት የተሰጠው ግለስብ በተመድ ከተሰየመው የአንድነት መንግስት ጋር እንዳይተባበር የሚያሳስብ ሲሆን ተባባሪ ሆኖ ከተገኘ ከፍተኛ እርምጃ እንደሚወሰድበት ይገልጻል። ሚስተር ካሊፋ ገውሊ በተመድ የተቋቋመውን የአንድነት መንግስት በጽኑ ከሚቃወሙ ግለሰቦች መካከል አንዱ መሆናችው የሚታወቅ ሲሆን መግለጫቸው በሌሎች ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት እንዳለው ለጊዜው ለማወቅ አልተቻለም። በአሁኑ ወቅት ሚስተር ካሊፋ ይህንን እርምጃ እንዲወስዱ የገፋፋቸው ምክንያቶች ለጊዜው ግልጽ ባይሆኑም በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ ክፍፍል መኖሩን ያሳያል በማለት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ።
Ø የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር ለቢቢሲ ጋዘጠኛ በሰጡት ቃለ ምልልስ የአሁኑ የስልጣን ዘመናቸው በ2013 ዓም ሲያልቅ ስልጣናቸውን የሚያስረክቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ስልጣን የሚለቁ መሆናቸውን በመግለጽ የገቡትን ቃል በተደጋጋሚ ሲያጥፉ የነበሩ በመሆናቸው እለቃለሁ ብለው መናገራቸው የተለመደው ማጭበርበር ነው  የሚሉ በርካታ ናቸው። ፕሬዚዳንቱ በቃለ ምልልስ ወቅት በዳርፉር ከ10 ሺ በላይ ዜጎች ቤታቸው ጥለው ተሰደዋል፤ 2.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በካምፕ ውስጥ ይኖራሉ  በሚል ተመድ ያሰራጨው መረጃ የተጋነነ ነው ከማለታቸውም በላይ የተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በዳርፉር የሚቆዩበት ምንም ምክንያት ስለሌለ ባስቸኳይ መውጣት አለባቸው ብለዋል። የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለፖሊቲካ ማራመጃ ተብሎ የተቋቋመ መሆኑን በመግለጽ በአገራቸው ሕዝብ ተወዳጅነት ስላላቸው የተመሰረተባችውን ክስ እንደማይቀበሉት በቃለ ምልልሱ ገልጸዋል።
  • በተያያዘ ዜና ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ከሳልቫ ኪር ጋር ከጥቂት ወራት በፊት እርቅ የተፈራረሙት ሪክ ማቻር በሚያዚያ 10 ቀን 2008 ዓም ጁባ የሚገቡ መሆናቸውንና በዚያም ከሳልቫ ኬር ጋር በመሆን የአንድነነቱን የሽግግር መንግስት እንደሚያቋቁሙ ገልጸዋል። ባሁኑ ጊዜ በአንዳንድ ቦታዎች የሚደረጉት ጦርነቶች ሙሉ በሙሉ ያልቆሙ በመሆናቸው ስምምነት የተደረገበት የአንድነት መንግስት ስራ አለመጀመሩ ብዙዎችን ሲያሳስብ ቆይቷል። በሌላ በኩል በደቡብ ሱዳን  መድኃኒት እና ሌሎች የህክምና አገልግሎት መሳሪያዎች ከፍተኛ እጥረት በመፈጠሩ ርዳታ ፈላጊዎችን ለመርዳት አዳጋች እየሆነ መምጣቱን ድንበር የለሽ ሃኪሞች የተባለው ድርጅት ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 29 ቀን 2008 ዓም በሰጠው መግለጫ ገልጿል። መግለጫው የእርዳታ ድርጅቶችና ሌሎች የአለም አቀፍ ተቋሞች ይህን ከፍተኛ የሆነ እጥረት ለማሟላት ባለመቻላቸው የብዙ ሰዎች ህይወት አደገኛ ሁኔታ ላይ ሊወድቅ ችሏል ብሏል።  የአለም የምግብ ፕሮግራም እና የዓለም አቀፉ የእርሻ እና የምግብ ድርጅት ማክሰኞ መጋቢት 27 በሰጡት መግለጫ በደቡብ ሱዳን የእርዳታ እህል እጥረት በመኖሩ ከፍተኛ ረሃብ እየተከሰተ መሆኑን የገለጹ መሆናቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment