Wednesday, April 6, 2016

ግብጽ ለኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎች የተለየ ድጋፍ አላደረግኩም አለች

ባሳለፍነው ወር 1000 የሚደርሱ በካይሮ የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን የኦሮሞ ተወላጆች የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ የተመሰረተበትን ሁለተኛ ዓመት በድምቀት ማክበራቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ግብጽ ተቃዋሚዎችን ማደራጀት ጀምራለች የሚል ስሞታ በማቅረባቸው ግብጽ ማስተባበያ አውጥታለች፡፡

Zehabesha News

በህዳር ወር የኦሮሞ ወጣቶች በኢትዮጵያ ከጀመሩት ህዝባዊ ተቃውሞ በኋላ በካይሮ ደመቅ ያለ ዝግጅት በስደተኞች ሲደረግ የካይሮው የመጀመሪያ በመሆን ተመዝግቧል፡፡ህዝባዊ ተቃውሞው በተቀጣጠለበት ወቅትም የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር መስሪያ ቤት አውጥቶት በነበረው መግለጫ ‹‹ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ግብጽ ጣልቃ አትገባም››ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ግብጽን በአገር ውስጥ ጉዳያቸው ጣልቃ እንደምትገባ በመግለጽ ውንጀላ ሲያቀርቡ የመጀመሪያቸው አለመሆኑን ያስታወሰው መረጃውን ይፋ ያደረገው ጋዜጣ በ2002 በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በሆስኒ ሙባረክ አስተዳደር ላይ በተደጋጋሚ ስሞታ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ተናግሯል፡፡
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክን የምስረታ በዓል በካይሮ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጅ ስደተኞች በድምቀት ማክበራቸውን ተከትሎ ግብጽ ለተሰነዘረባት ወቀሳ ስማቸውን በቃለ አቀባይዋ በኩል በሰጠችው ማስተባበያ ‹‹ከዝግጅቱ ጋር የግብጽን ባለስልጣናት የሚያገናኛቸው ምንም ነገር የለም ››ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
ባለስልጣኑ ‹‹ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን አክቲቪስቶች ለዝግጅቱ የደህንነት ዋስትና እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ይህም በካይሮ ለሚገኙ የሌሎች አገራት ስደተኞች የምናደርገው በመሆኑ የተለመደ ነው፡፡ግብጽ በአለም አቀፍ ደረጃ የገባቻቸውን ውሎች በማክበር የምትፈጽም በመሆኗም ስደተኞች በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር የገቡ ቢሆኑም ብሄራዊ አደጋ እስካልሆኑ ድረስ ከለላ ታደርግላቸዋለች››ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

No comments:

Post a Comment